26/08/2021
ከጽዳት ሠራተኛነት የጌጣጌጥ ድርጅት እስከ መመስረት!
እየሩሳሌም ቀንዓ ትባላለች የሊሉያን ድርጅት ባለቤት ናት። ሉልያን በፋሽን ጌጣጌጥ ምርቶች እንዲሁም በቆዳ ምርቶች ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው።
እናቷ እና አባቷ ተለያይተው በእናቷ እጅ ያደገችው እየሩሳሌም፣ የእናቷን የእደጥበብ ሙያ ብቻ ሳይሆን የኑሮ ውጣ ውረዳቸውም በርካታ ነገሮችን እንድትቀስም አድርጓታል።
እናቷ እርሷን ሲያሳድጉ ቤት ውስጥ ብቻዋን ጥለዋት መውጣት ከባድ ፈተና ሆኖባቸው የነበሩባቸውን ጊዜያቶች ታስታውሳለች።
በልጅነቷ ወቅት ቤተሰቦቿ ከጎረቤት እንዲሁም ከሞግዚት ጋር ትተዋት በሄዱባቸው ወቅቶችም የተለያዩ አካላዊ፣ ስነልቦናዊ ጥቃቶችን ማስተናገዷንም እንደዚሁ።
የእየሩሳሌን እናት የተመሰከረላቸው የእደ ጥበብ ባለሙያ ነበሩ።
ከልጅነቷ ጀምሮ የልብስ ቅድና ስፌት ሙያን ከእርሳቸው እጅ ተምራለች። በአራት ዓመቷም ከፌስታል ቦዲ መስራቷን ትናገራለች።
እየሩሳሌም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመግባት እና ለመማር ባለመቻሏ ጽዳት ከመሥራት ጀምሮ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች።
ዩኒቨርስቲ ከገባች በኋላም በቀንና በማታው የትምህርት ክፍል በመማር ሁለት ዲግሪዎችን ሠርታለች።
እነዚህን ዲግሪዎች ስትሰራ ግን የትምህርት ወጪዋን ትሸፍን የነበረው እየሰራች ትሸጣቸው በነበሩት ጌጣጌጦች ነው።
የኮሌጅ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ የተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርታ እንደነበር የምትናገረው እየሩሳሌም፣ ከዚያም ሊሉያንን በመመስረት የእደጥበብ ውጤቶችን የዕለት ተዕለት ሥራዋ እና ቋሚ ገቢ የምትገኝበት ዘርፍ አደረገችው።
ሊሉያን በግዕዝ ልዩ ሕዝብ ማለት ነው።
እየሩሳሌም አፍሪካውያኖች ልዩ ሕዝቦች ነን ስትል ትገልጻለች።
ከሌላ ዓለም የምንቀዳው ነገር በጣም አነስተኛ ነው የምትለው እየሩሳሌም፤ የራስን መልክ፣ የራስን ውበት፣ የራስን ማንነት ለማጉላት ደግሞ ያልተነካ እምቅ ሃብት በአፍሪካ መኖሩን ትናገራለች።
እየሩሳሌም የምትሰራቸው ጌጣጌጦች የአንገት ሐብሎች፣ ቀለበቶች፣ የጆሮ ጌጦች እና አምባሮች ናቸው።