05/06/2026
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ሂደት ላይ ያለውን ምልከታ ይፋ አደረገ
[ሸገር አዲስ ሚዲያ ግንቦት 28/2018]
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ወቅት ያከናወነውን አገር አቀፍ የታዛቢነት የክትትል ሥራ ሪፖርት እና የሚዲያ መግለጫ በአዲስ አበባ ሰጥቷል።
ፌደሬሽኑ በመላ አገሪቱ ከ14 ሺህ በላይ ታዛቢዎችን በመመደብ፣ ከ25 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎችን መሸፈን መቻሉን አስታውቋል።
ከተመዘገቡት አጠቃላይ መራጮች ውስጥ የሴቶች ቁጥር 49.3 በመቶ መድረሱ እና የባዮሜትሪክ የቴክኖሎጂ ምዝገባ ለመጀመሪያ ጊዜ መተግበሩ በምርጫው የታዩ ዋና ዋና ጥንካሬዎች መሆናቸውን ፌደሬሽኑ ገልጿል።
በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል የምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ አለመክፈትና በአንዳንድ አካባቢዎች በሴት መራጮች ላይ የተስተዋሉ ጫናዎች፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያጋጠሙ የጸጥታ ስጋቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ የታየው የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት አለመቀናጀት በሂደቱ ላይ የታዩ ተግዳሮቶች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ፌደሬሽኑ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችን ለመከላከል የጸጥታ አካላትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል። በቀጣይም የምርጫ አስፈጻሚዎች በቂ ስልጠና እንዲያገኙ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢያንስ 30 በመቶ የእጩዎች ቁጥር ለሴቶች እንዲያደርጉ ምክረ-ሃሳቡን አቅርቧል።