15/03/2026
ታሪካዊው የ #ዋራቤቴል 2018 ጉባኤ በበዓለ ሃምሳ ዕለት በኢየሱስ ስም ከተጠመቁት በአራት እጥፍ ከ12 ሺህ በላይ ነፍሳት በኢየሱስ ስም በማስጠመቅ ተጠናቀቀ
ለአራት ተከታታይ ቀናት በሲዳማ ክልል ዋራ ሜዳ ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ሲሳተፉበት የነበረው 35ኛው የአለም አቀፍ ሐዋሪያዊት ቤተክርስቲያን ታላቅ ዓመታዊ ኮንፈረንስ ( #ዋራቤቴል) በዛሬው ዕለት በታላቅ መንፈሳዊ ስኬትና በሰላም ተጠናቋል።
ከባለፈው ሐሙስ ጀምሮ እስከ ዛሬው የማጠቃለያ ዕለት ድረስ በነበረው መንፈሳዊ አገልግሎት፣ 12,296 (አሥራ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ስድስት) ነፍሳት ብቻውን አምላክ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመንና ለኃጢአታቸው ስርየት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቃቸው ታውቋል።
ይህ ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሁለት ላይ፣ በበዓለ ሃምሳ ዕለት በኢየሱስ ስም ከተጠመቁት ሦስት ሺህ ሰዎች በላይ በመሆኑ፣ ጉባኤው በዘመናችን የታየ ታላቅ ተአምርና መንፈሳዊ መነቃቃት ተደርጎ ተወስዷል።
በዋራ ሜዳ ላይ የተከናወነውን ይህን ታላቅ መንፈሳዊ ድልና ተአምራት ተከትሎ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩ ምዕመናን ለፈጣሪያቸው ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል።
በደዌና በአጋንንት እስራት የነበሩ መፈታታቸውንና በንስሐ ወደ አምላካቸው የተመለሱት ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ጉባኤውን ልዩ ያደርገዋል።
ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ደረጃ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሕዝብ ያለ ምንም የዘርና የነገድ ልዩነት ከየአቅጣጫው በአንድነት የሚሰበሰብበት ብቸኛ ቦታ ነው ማለት ይቻላል።
ያለ ምንም የዘርና የነገድ ልዩነት ከዓለም ዙሪያ የመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ ልብ አምላካቸውን ያመሰገኑበት ይህ ጉባኤ፣ ለሲዳማ ክልልም ሆነ ለኢትዮጵያ የሰላምና የመቻቻል ትልቅ ማሳያ ሆኖ አልፏል።
ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር፣ ክልሉን ለዓለም በማስተዋወቅና የቱሪዝም አቅምን በማሳደግ ረገድም ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
የአለም አቀፍ ሐዋሪያዊት ቤተክርስቲያን አመታዊ ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት በሰላም መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ምዕመናን ወደየመጡበት አካባቢ በመመለስ ላይ ይገኛሉ።
#ዋራቤቴል #ኢትዮጵያ