28/02/2026
ሰበር ዜና: አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ሲፈፅሙ በቴህራን በርካታ ፍንዳታዎች ደረሱ
ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ኢራን ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፣በቴህራን ዙሪያ በርካታ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል። በርካታ ሚሳኤሎች በቴህራን ዩኒቨርሲቲ ጎዳና እና ጆምሁሪ አካባቢን መምታታቸውን የፋርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። በከተማዋ ውስጥ ጭስ እየጨመረ ሲወጣ ታይቷል።
የእስራኤል የመከላከያ ሚንስትር ኢዝራኤል ካትስ እስራኤል የሚሳኤል ጥቃቱን የከፈተችው "በእስራኤል መንግስት ላይ የሚደርሰውን ስጋት ለማስወገድ" ነው ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን ለአልጀዚራ እንደተናገሩት ጥቃቱ የተፈፀመው በእስራኤል እና በአሜሪካ መካከል በተደረገው የጋራ ወታደራዊ ዘመቻ ኢራንን በኒውክሌር መርሃ ግብር ስምምነት ላይ እንድትደርስ ጫና ለመፍጠር በቀጣናው በርካታ ተዋጊ ጄቶች እና የጦር መርከቦችን በማሰባሰብ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
አሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደዘገበው በኢራን ዋና ከተማ ጥቃቱ የተፈፀመው በጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ካሚኒ ቢሮዎች አቅራቢያ ነው። ሮይተርስ በበኩሉ እንደዘገበው ካሜኔ ቴህራን ውስጥ የሉም እናም ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ አቅንተዋል ብሏል። የኢራን ከፊል ይፋዊ የዜና ወኪል ታስኒም እንደዘገበው በቴህራን ሰሜናዊ ሴይድ ካንዳን አካባቢ ፍንዳታዎችም ተከስተዋል።
የኢራንን የአፀፋ እርምጃ በመስጋት የእስራኤል ኤርፖርቶች ባለስልጣን የአየር ክልል ለሁሉም ሲቪል በረራዎች መዘጋቱን እና ህዝቡ ወደ አየር ማረፊያው እንዳይመጣ አሳስቧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በኳታር የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ለሁሉም ሰራተኞች የመጠለያ ቦታን ተግባራዊ አድርጓል፣ ይህም ሁሉም ዜጎቹ ተጨማሪ ማሳወቂያ እስኪደርሳቸው ድረስ ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ መክሯል።
ሮይተርስ የእስራኤል የመከላከያ ባለስልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው ጥቃቱ ለወራት ታቅዶ እንደነበር እና የሚጀመርበት ቀን ከሳምንታት በፊት ተወስኗል ብሏል።