16/08/2026
በዳውሮ ዞን በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር ሲያሰራጭ የነበረ ግለሰብ በእስራት ተቀጣ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዳውሮ ዞን ማሪ ማንሳ ወረዳ በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር ሲያሰራጭ የነበረ ግለሰብ በጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የዳውሮ ዞን ፖሊስ መምሪያ የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ዲቪዥን ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አሰራት ዶግሶ እንደገለጹት፣ ተከሳሹ ማቴዎስ ባቡሎ በየኔ የተባለ ግለሰብ በማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም በኦርቶዶክስ እና በፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች መካከል መቃቃር እና ጥላቻ እንዲፈጠር የሚያደርጉ የጥላቻ ንግግሮችን ሲያሰራጭ ተደርሶበታል።
የቀረበውን የወንጀል መዝገብ እና ማስረጃ የተመለከተው የማሪ ማንሳ ወረዳ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ የተሰነዘረውን የጥላቻ ንግግር ወንጀል መረጋገጡን ተከትሎ፣ ተከሳሽ ማቴዎስ ባቡሎ በየኔ በአንድ ዓመት ከሁለት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎበታል።
ፖሊስ አክሎም ህብረተሰቡ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ አላማ ብቻ እንዲጠቀም እና በሃይማኖቶች መካከል ልዩነት እና ግጭት የሚፈጥሩ ድርጊቶችን ከመፈጸም እንዲቆጠብ አሳስቧል።