21/08/2026
«ዮ__ማስቃላ»
የጋሞ ብሄረሰብ የዘመን መለጫ በዓል
በጋሞ ዞን በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀውን «ዮ ማስቃላ» የዘመን መለወጫ በዓልን በድምቀት ለማክበር ሁሉም በየፈርጁ ዝግጅቱን ቀደም ብሎ ይጀምራል።
«ዮ ማስቃላ» በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ቅበላው ተከብሮ በታህሳስ ወር መጨረሻ የ«ማስቃላ» ሽኝት በዓል በድጋሚ በድምቀት ይከበራል።
በዞኑ በተለያዩ ማህበራት በመደራጀት ገንዘብ የማሰባሰብ ዝግጅት የሚጀምሩት ቀደም ብሎ ነው። በዚሁ መልኩ ዓመቱን ሙሉ ገንዘብ በመቆጠብ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ይደረጋል።
ይህ ተግባር በሁለቱ ፆታዎች የሚከናወን ዝግጅት ሲሆን ወንዶች ለበዓሉ የሚሆን ሠንጋ መግዣ፣ ለልጆች ልብስ እና ጌጣጌጥ ማሟያ፤ እናቶች ደግሞ በበኩላቸው ለቅቤ፣ ለቅመማ ቅመም፣ ለባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች እህል መግዣ የሚሆን ገንዘብ ማጠራቀም ያጠራቅማሉ።
ለማስቃላ በዓል የሚዘጋጁ ተወዳጅ ባህላዊ ምግቦች መካከል የገብስ ቅንጬ፣ ከቡላ ቆጮ እና ገብስ የሚዘጋጅ ቂጣ፣ የቡላ ፍርፍር፣ የሐረግ ቦዬ ሲሆኑ ቦርዴ፣ የማርና የቦርዴ ውህድ የመሳሰሉ ባህላዊ መጠጦችም በስፋት ይዘጋጃሉ።
በጋሞ ዞን የማስቃላ በዓል ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንሳስት እና ለአዕዋፋም ጭምር ነው ተብሎ ይታመናል፤ በዕለቱ ምግብ ከሰው አልፎ ለእንሳስት እና ለአዕዋፍም ይትረፈረፋል። ለከብቶችም የግጦሸ መሬት በየአካባቢው ይከለላል።
በተለያዩ አጋጣሚዎች የተጣሉ ታርቀው፣ የተራራቁ ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆች ተሰባስበው በዓሉን በጋራ እንዲያከብሩ ማድረግ የጋሞ ማስቃላ በዓል መገለጫ ነው።
መስከረም ወር የመጀመሪያው ቀን በጋሞ ዞን ”ሂንግጫ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህም አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዝግጀት የሚደረግበት ቀን ነው። የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ የገበያ ቀናትም ይገኛሉ።
ከገበያ ቀናቱ መካከል
• “ጋሜ ጊያ” የእርድ ከብቶች እና ለማስቃላ በዓል የሚሆኑ ልዩ ልዩ ቁሳቁስ የሚገዛበት ነው፤
• “ዩሼ ጊያ” ወላድ እናቶች በማስቃላ በዓል ገበያ ወጥተው ዘና የሚሉበት ነው፤
• “ጎሻ ጊያ” የማስቃላ ዝግጅት ካበቃ በኋላ የመጨረሻው ገበያ ሆኖ እንደ ቅመማቅመም የመሳሰሉ ጥቃቅን ነገሮች የሚሸምቱበት እና ፈጥነው የሚመለሱበት በመሆኑ እንደወትሮው የደራ ገበያ አይሆንም።
ለ«ዮ…ማስቃላ» የሚደረጉት ዝግጅቶች ከተጠናቀቁ በኃላ ቀደም ሲል ለሶስት ወር ያህል ተከልሎ የቆየው የግጦሽ መሬት ለከብቶች ልቅ ይሆንና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በዓሉን ማክበር ይጀምራሉ።
በጋሞ ዞን የማስቃላ የእርድ ሥነ-ሥርዓት ከቦታ ቦታ ይለያያል። የመጀመሪያው በደመራው ዕለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በማግሥቱ ይፈፀማል።
እርዱ በየቡድኑ በተደራጁ ቤተ-ዘመዶች ወይም ጎረቤቶች ገበያ ላይ አልያም አማካይ በሆነ ቦታ ይከናወናል።
ከቡድኑ አባላት ሴቶች ቦርዴ እና ማባያ ይዘው በእርዱ ቦታ ይገኛሉ።
ከየሥጋው ዓይነት የተመተረውን ተሰባስበው ከቀማመሱ እና በቦርዴ ካወራረዱ በኋላ የድርሻቸውን ሥጋ ተከፋፍለው ይለያያሉ። ወደ ቤት እንደደረሱም ቤተሰብ ተሰብስቦ ቁርጥ ሥጋ ይበላል።
ከሰዓት በኋላ ወይም ማታ ለሁሉም ቤተሰብ የሚበቃ ጎረድ ጎረድ በቅቤ ተለውሶ በትልቅ ወጭት ላይ ቀርቦ በባህላዊ ማንኪያ ይበላል።
በ2ኛው እና በ3ኛ ቀናት ጎድን ጥብስ በቂጣ ይበላል። ከሐረግ ቦዬ ብቻ የሚዘጋጅ ተሰርቶ ዮ...ዮ...ማስቃላ በመባባል ለሚመጡ ሰዎች ከባህላዊ መጠጥ ጋር ሣምንቱ እስኪያልቅ ድረስ ይቀርባል።
በባህሉ መሠረት ችቦ የሚወጣበት ሰዓት ሲደርስ አባት የራሱን ችቦ ለኩሶ የቅቤ ምንቸቱን፣ የቤቱን ምሰሶ፣ የከብቶቹን ጋጣ እና የበር ጉበኖችን ግራ እና ቀኝ በችቦው ጫፍ ያነካካል።
ከዚያም ወደ ውጪ ሲወጣ ወንድ ልጆች የየራሳቸውን ችቦ ተራ በተራ እየለኮሱ እና አባትን ተከትለው ዮ..ዮ..ማስቃላ እያሉ በመጨፈር ወደ ደመራው ቦታ ከደረሱ በኋላ አባት በቀዳሚነት ልጆች ደግሞ በተከታይነት ደመራውን ይለኩሳሉ።
በዕለቱ የሚዘጋጀው ባህላዊ ምግብ ገንፎ ሲሆን ይህንን ወንዶች ከጭፈራ ሲመለሱ ተሰባስበው ከአንድ ወጭት ዮ...ዮ ማስቃላ እያሉ ሁሉም የቤተሰብ አባላት፣ ዘመድ አዝማድ እና ጎረቤቶች ያለ ልዩነት በጋራ ይመገባሉ።
በጋሞ ብሔረሰብ የሚከበረው የማስቃላ በዓል በሶፌ ሥርዓት የታጀበ ነው።
የቀደመው ዓመት ማስቃላ በዓል ከተከበረ በኃላ የተጋቡ ሙሽሮች ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ማምሻውን በአደባባይ ከመላው ህብረተሰብ ጋር የሚቀላቀሉበት እና ሁለቱም ተጋቢ ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው ደስታቸውን የሚገልፁበት ሥርዓት ነው።
በዚህ ወቅት የሚወጡ ሙሽሮች በተለያዩ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ ተውበው ስለሚታዩ እንደቁንጅና ውድድር የተመልካችን ትኩረት ይስባል።
የመጨረሻው የማስቃላ ሽኝት በዓል ነው፤ ይህ ሥርዓት እንደየአባወራው አቅም በፈቀደ መጠን የሚፈፀም ነው። በዚህ ዕለት ሁሉም ያለ ፆታ ልዩነት በአደባባይ ላይ ወጥተው ያኑረን እስከ ወዲያኛው እንኖራለን እያሉ ይጨፍራሉ።
ከዚህ በኋላ ለመጪው ዓመት በሠላም በጤና ያድርሰን ተባብለው ፈጣሪን በመማፀን ዝግጅቱ ይቋጫል።
« ዮ ማስቃላ!»
Via ጋሞ ዞን ቱሪዝም መምሪያ