ኪነ ሂስ Kine Hise

ኪነ  ሂስ Kine Hise ይህ ገጽ የኪነ ጥበብ ስራዎች(ቴአትር፣ ግጥም፣ አጭርና ረዥም ?

~~~ዋ!... ያቺ አድዋ~~~(የአለም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን)ዋ!...አድዋ ሩቅዋየዓለት ምሰሶ ጥግዋሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋአድዋ…ባንቺ ህልውናበትዝታሽ ብጽዕናበመሥዋዕት ክንድሽ ዜናአበው ታ...
01/03/2026

~~~ዋ!... ያቺ አድዋ~~~
(የአለም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን)

ዋ!...
አድዋ ሩቅዋ
የዓለት ምሰሶ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ

አድዋ…
ባንቺ ህልውና
በትዝታሽ ብጽዕና
በመሥዋዕት ክንድሽ ዜና
አበው ታደሙ እንደገና…

ዋ!
አድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ሥርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰዉብሽ ለት፤

አድዋ
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ
የኢትዮጵያነት ምስክርዋ

አድዋ
የኩሩ ደም ባንቺ ጽዋ
ታድማ በመዘንበልዋ
ዐፅምሽ በትንሣኤ ነፋስ
ደምሽ በነፃነት ሕዋስ
ሲቀሰቀስ ትንሳኤዋ
ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ
ብር ትር ሲል ጥሪዋ
ድው-እልም ሲል ጋሻዋ
ሲያስተጋባ ከበሮዋ
ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ
ያባ መቻል ያባ ዳኘው
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው
ያባ በለው በለው ሲለው
በለው-በለው-በለው-በለው!

ዋ!... አድዋ…
ያንቺን ጽዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ በለው፣ በለው- በለው!

ዋ! … አድዋ …
አድዋ የትላንትናዋ
ይኸው ባንቺ ህልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመሥዋዕት ክንድሽ ዝና
በነፃነት ቅርስሽ ዜና
አበው ተነሡ እደገና፡፡

… ዋ! … ያቺ አድዋ
አድዋ ሩቅዋ
የዐለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
አድዋ…

24/09/2025
02/03/2019

(ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን)
ዋ! ..... ያቺ ዓድዋ
ዋ! ...
ዓድዋ ሩቋ፣
የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋቋ፣
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋቋ።
ዓድዋ.....
ባንቺ ብቻ ሕልውና፣
በትዝታሽ ብፅዕና፣
በመስዋዕት ክንድሽ ዜና፣
አበው ታደሙ እንደገና።
ዋ!
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስቷ፣
የደም ትቢያ መቀነቷ።
በሞት ከባርነት ሥርየት፣
በደም በነፃነት ስለት፣
አበው የተሰውብሽ ለት።
ዓድዋ!
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ፣
የኢትዮጵያነት ምስክርዋ።
ዓድዋ
የኩሩ ደም ባንቺ ጽዋ፣
ታድማ በመዘንበልዋ።
ዐፅምሽ በትንሳኤ ንፋስ፣
ደምሽ በነፃነት ሕዋስ።
ሲቀሰቀስ ትንሳኤዋ፣
ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ፣
ብር ትር ሲል ጥሪዋ፣
ድው እልም ሲል ጋሻዋ፣
ሲያስተጋባ ከበሮዋ፣
ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ።
ያባ መቻል ያባ ዳኘው፣
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው፣
ያባ በለው በለው ሲለው፣
በለው በለው በለው በለው።
ዋ! ...... ዓድዋ .....
ያንቺን ፅዋ ያንቺን አይጣል፣
ማስቻል ያለው አባ መቻል።
በዳኘው ልብ በአባ መላው፣
በገበየሁ በአባ ጎራው፣
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው፣
በለው ብሎ በለው በለው።
ዋ! ...... ዓድዋ .....
ዓድዋ የትናንትናዋ፣
ይኸው ባንቺ ሕልውና፣
በትዝታሽ ብፅዕና፣
በመስዋዕት ክንድሽ ዝና፣
በነፃነት ቅርስሽ ዜና፣
አበው ተነሱ እንደገና።...... ዋ! ........ ያቺ ዓድዋ፣
ዓድዋ ሩቅዋ ፣
የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ፣
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ።
ዓድዋ .......
የካቲት - (፲፱፻፷፬ -ዓድዋ)
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን/
¶ ዓድዋ ¶

14/02/2019

ለስነ ሂስ ኮርስ ማሟያ
ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ ልቦለድ

በፍቅር አምሳሉ

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
የስነ ጥበባት ኮሌጅ
የቲያትር ትምህርት ቤት
አዲስ አበባ
2ዐ11 ዓ.ም
እነሆ ለስነ ሃስ ኮርስ ማሟያ የሰራሁት ይወስዳል መንገድ ያደርሳል መንገድ ልቦለደ ላይ የተሠራ ሂስ ሲሆን አንብባችሁ ገንቢ አስተያየት እንደምትሰጡኝ በመተማመን ለእናንተ አጋርቻለሁ መልካም ንባብ
ደራሲ አዳም ረታ
ርዕስ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ (የሰባት መንገዶች ወግ)
የታተመበት (2ዐዐ3- 2ዐዐ5)
የመጽሐፉ ዋጋ በአሁኑ ሰዓት 12.ዐዐ
የገጽ ብዛት 438.ዐዐ
መግቢያ
ደራሲ የተፈጠረበት ማህበረሰብ አባል እንደመሆኑ መጠን የማህበረሰቡ አኗኗር ባህል ተጋሪም ነው፡፡ የስነ ፅሁፍ ሥራውም በአንድም ይሁን በለላ የማህበረሰቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ እውነት ነፀብራቅ ነው በረቀቀ አገላለፅ ስልት፣ በልዩ የቃላት ቀመር የማቅረብ ችሎታው እንደ ደራሲው ብቃትና ብስለት የሚወሰን ቢሆንም እውነታው ግን የሚቀዳው ከዕለት ተዕለት የሰዎች መስተጋብር ነው፡፡
የኖርንበትንና ያለንበትን ዘመን ከሌላው ማህበረሰብ በተለየ መነፅር የማየት ልዩ ብቃት ባለቤትም ነው፡፡ የታየውን በተሻለ ጥልቀት ማሳየት ወይም የተደበቀውን ፈልፍሎ የማውጣትና የማሳወቅ ችሎተውም በስነ ፅሁፍ ሥራው ላይ ይንፀባረቃል በዙሪያው የሚያየውንና የሚሰማውን፣ በምናብ ከሚፈጥረው እውነት ጋር አስማምቶና አዋህዶ የሚፅፈው መነሻው የገሃዱ አለም የማህበረሰብ፣ የሀገር እውነት መሆኑ ነው፡፡
ይዘት
ደራሲ አዳም ረታ በ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ልቦለዱ ላይ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አሳይቷል፡፡ በዚህ ልቦለድ በሀገራችን ውስጥ በአንድ ዘመን ሆኖ ያለፈን የአንድ ትውልድ ታሪክ ከውልደት እስከ ስደት ያስቃኛል፡፡ ከአንደኛው መንገድ እስከ ሦስተኛው መንገድ የገፀሰቡን ከልደት እስከ ጉርምስና ዕድሜ ያለን የህይወት ጉዘት በጣም በጥልቀት እንቅስቃሴውን እያሳየ ማህበረሰቡ የነበረውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዉ ትስስር የሚያሳይ ነው፡፡
በዘመኑ የነበሩ የቤት ዓይነቶች የጉርብትና ጥግ፣ የኑሮ ደረጀ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሀይማኖት ልማድ ወዘተ… ከአፈር ጋር (ከመንገድ) ጋር ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝት ኑሮን ለማሸነፍ የሚደረግን ትግል የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የበረውን መስተጋብር ደራሲው በጥልቀት አቅርቧል፡፡
ተራኪው በአንደኛ መደብ የሚተርክ ሲሆን፣ ገፀ ሰቡ ከመንገድ ጋር ( ከአቧራ ጋር ያለውን የጠበቀ ቁርኝት ወደ ዚህች ዓለም ሲመጣ ከእናቱ ማህፀን ሲወጣ የልምድ አዋላጆች በመጥ ከምትወራጨው እናቱ ራስጌና ግርጌ ሆነው ከቀሚሳቸው ግርጌ ከሚቦነው አቧራ ጀምሮ እሱ ወደ ዚህች ዓለም ሲቀላቀል (ሲወለድ) እና እትብቱ ሲቆረጥ በቁስሉ ላይ አርፎ አብሮት የደረቀውን አቧራ ጭምር እናስተውላለን፡፡ በዚህም አቧራው ከአሱነቱ ጋር የለው ግንኙነት የደምና የሥጋን ያህል የተዋሃደ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እያደገ ሲሄድም ከምግቡ ጋር ከልብሱ ጋር ከመኝታው እስትንፋሱ ሁሉ ሳይቀር አቧራ አዘል ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ይህ በዚያን ዘመን የበሩ ኢትዮጵያዊያንን አብዛኛውን ህይወት ያሳያበት ነው፡፡ አብዛኛው ከአቧራ ጋር ይወለዳል፣ ከአቧራ ጋር ይኖራል…….፡፡
“ይወስዳል መንገድ ያመጣል ልቦለድ” አጠቃላይ ይዘት የአንድ ዘመን 195ዐዎቹ - 7ዐዎቹ የኢትዮጵየን ሀይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ኩነቶች በጥልቀት የተዳሰሱበት የድርሰት ሥራ ሲሆን ደሪሲው አዳም ረታ እንደ ቀደምት ሥራዎቹ በልዩ የአፃፃፍ ስልቱ በሀገራችን የሥነ ፅሁፍ ታሪክ ላየ ተጨማሪ አሻራውን ያሳረፈበት ነው፡፡
በደራሲ አዳም ረታ ለህትመት የበቁ ልቦለድ መጻህፍትና አንባቢ ዘንድ የደረሱ እንዲሁም ከነዚህ መካከል በሬዲዮ የተተረኩ ሥራዎቹ
- ግራጫ ቃጭሎች 1997 በሬዲዮ የተተረከ
- አለንጋና ምስር 9ዐዐ1
- እቴሜቴ ሎሚሽታ (2ዐዐ1) ወደ ፊልም የተቀየረ
- ማህሌት (1981 2ዐዐ2) እንደገና የታተመ
- ከሰማይ የወረደ ፍርፍር (2ዐዐ2)
- ህማማትና በገና (2ዐዐ4)
ይህቺኛዋ መንገድ ሁለተኛዋን አትሽርም፡፡ /ልደት/
ገፀ ሰቡ (ዓለሙ) በሁለተኛው መንገድ ከህፃንነት ወደ አፍላነት የተሸጋገረበት ዕድሜ ላይ ሆኖ በእሱ እድሜ የተለወጡትን አካላዊ አዕምሮአዊ ስነ ልቦናዊ ለውጥ ያሳየናል ጐን ለጐንም የነበረውን ማህበረሰባዊ ቁርኝት የኑሮ ሁኔታ በሀዘን፣ በደስታ፣ በችግር፣ በተድላ ጊዜ አንዱ የሌላውን ገመና የሚሸፍን፣ ያንደኛዋ ጓዳ የሌላኛዋ እንደነበር በግልፅ ያንፀባርቃል፡፡ የስማት ፍቅርቆሽሽ፣ ከጥልቀት የሀዘን ስሜት ሰዐታት ቀናት ቢፈጅም ወጥቶ ወደ ጥልቅ ደስታ ሳቅ በመግባቱ ራሱን ይታዘባል፡፡ ይኼ ስሜት ግን የሰው ልጅ ሁሉ የሚጋራው ስለሆነ ገፀ ሰቡን ስርዓት አልበኛ አልያም ወግ የጣሰ አያደርግውም፡፡ ለሁለት ሳምንት የቆየ የዓለሙን ህልመ ስናነብ ህልመ ከአነድ ጊዜ በላይ እየተመላለሰ የመታየት ልምድ በማህበረሰቡ ዘንድ እንደ ቅዥት እንደሚቆጠር እና ያልተለመደም መሆኑን ነግሮናል፡፡ ሆኖም “ በልጅ ይታየዋል” የሚባል ብሂልም ከሃይማኖታዊ “ ህፃናት ንፁሃን ናቸው፡፡ የሚል አገላለፅ ጋር ያለውን አንድነት ስናይ ሰዎቹ የክርስትና እምነት ተከታዩች መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ዓለሙ ለሁለት ሳምንት ያየው ህልምም በፍልሰታ ፆም ውስጥ (ጊዜው) መሆኑ ወደ ፊት ለሚመጣው ቀጣይ ታሪክ እንደ ትንበያም ሊሆን ይችላል፡፡ መንገዱ ቀጥሏል…..
ይህቺኛዋ መንገድ ያለፈችውን ሁለተኛዋን አትሽርም
ዓለሙ በእግሩ ድክ ድክ ማለት የጀመረበትን ለእሱ ዕድሜ የዓለም ስፋት የመሰለውን አካባቢውን በእግር የተጓዘበት የመንደር መንገድ፣ ክረምት ቦይ እየቀደደ፣ ሳር እያበቀለ ለመንገደኛው መተላለፊያ ሲያስቸግር፣ የህፃናቱ ጨዋታ፣ የአዋቂዎች እሮሮ፣ የተለያዩ ማህበረሰብ አካላት ውሎ በዓለሙ ትዝታ ውስጥ ትናንትን በሚያስታውስ መልኩ ግልፅ ሆኖ ይታያል ቄሶች፣ መምህራን፣ ጋሼ ሸገኔ፣ ልጃቸው ዋኖስ…. የጐረቤትን ልጅ እንደ ራስ ልጅ መቅጣት፣ በዘመኑ የበረ አዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ…… “ የመልካሙ ተበጀ ዘፈን፣ የፖለቲካ ሽኩቻ፣ ሀይማኖትን ወደ ጐን ትቶ በፖለቲካ መጠመዱን ይኼም በዘመኑ የነበረ እውት እንደ ነበረ እንረዳለን፡፡

ይህችኛዋ መንገድ ያለፈችውን ሦስተኛዋን አትሽርም
ዓለሙ በአራተኛው መንገድ ለይ የ 16 ዓመት ጎረምሳ ሆኖ በዘመኑ ፖለቲካ ተቃኝቶ ሌሎችን ማስፈራራት መንገድ ላይ ደርሶ ይታያል፡፡ በዚህ ዘመን “ አብዮታዎ እርምጃ” እየተባለ ሰዎች በሚያውቁትም በማያውቁም በግፍና በጅምላ ሲጨፈጨፉ የነበረበትን ጊዜ ያስታውሰናል፡፡
ማህበራዊ ኑሮው ህብረተሰቡ ደሃና ሀብታም ጎራ መለየት የጀመረበት ሰዎች ባለመኪና በመሆናቸው የሚከበሩበት፣ ልጃገረዶች ባለመኪና እንዲወዳቸው፣ ወይም እንዲያገባቸው የነበራቸው ፍላጐት፤ የሀገሪቱ ፖለቲካም በዕውቀትና በሳይንሰ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በስሜት በመነዳት ብዙ ህዝብ ያለቀባት፣ ፖለቲካውን ሽፋን በማድረግ ግብረገብነት የጠፋበት ስርዓት አልበኘነትም የተንሰራፋበት ወቅት ነበር፡፡ አራተኛው መንገድ በደም የተሠራ ነበር፡፡
ይሄ መንገድ አራተኛውን አይሽርም…… /የስደት መንገድ/
አምስተኛው መንገድ ጎፈሬ ማበጠር፣ የወዛዝርቱን ከፊል የተራቆተ ጭኖች ማየት፣ ከንፈሮች በቀለም ማቅላት ባለ ቀይ መብራት ጭፈራ ቤቶች የተበራከቱበት በሌላኛው ፅንፍ ህዝብ በጭቆና የሚቃዩበት፣ ተማሪዎች በየአካባቢያቸው የሚጨፈጨፉት ‘የተማሪ ንቅናቄ’ የሚባል አደረጃጀት ተማሪዎችን ከትምህርት ያሰናከለበት የማርክስ ፍልስፍና የተሰበሰበበት በዚህ ወቅት ሀገሪቱ ሁሉ በጨለማ ተውጣ እንደበር፣ በሞት ድገስ በደም አበላ ተጨማልቃ እንደነበር በዓለሙ ትዝታ ውስጥ ብናይም ሀገራችን የነበረችበት ነባራዊ እውነት እንደሆነ በታሪክ ተፅፏል፡፡ እናም ከተወለደበት ከተማ ርቆ ሄዶ የማያውቅ እግር በብሶት፣ በፍርሃት፣ ከተወለደበት ከተማ በብሶት፣ በፍርሃት፣ ለውጥ ፍለጋ፣ ከሀገሩ ይሰደዳ የብዙ ኢትዮጵያዊ የትናንት ታሪክ ያስታውሰናል፡፡
ይኼ መንገድ አምስተኛውን አይሽርም፡፡ /ቀዝቃዛ የስደት መንገድ/
ዓለሙና ጓደኞቹ አብሮ አደጎቹ ከትውልድ ቀዬያቸው ተሰድደው በባዕዳን መንደር እንኳን ተለያይተው የብቸኝነትን፣ የትዝታን ኑሮ ኑሮአቸው አድርገው በሀገራቸው ይመኙት የነበረውን እኩልነት ነፃነት የሚባል ፍልስፍና ከነስሙም አጥተውት በፈረንጅ ተልዕኮ ከሀገራቸው መሰደዳቸውን በቁጭት ያስታውሱታል፡፡ ዓለሙም “ከሩቅ ያዘኑልኝ የነበሩ የዴሞክራሲ መፃህፍት በጐዳና የገለሙ እርጎ ሆነው አገኘኋቸው፡፡ ለፃነት ይጮሁ የነበሩ ፖለቲከኞች በብልጠታቸው ስደተኛ አሉኝ፡፡ ‘ዓለም አንድ ናት’ ብለው የሰበኩኝ ወሰን እንዳለ ለአስተማሩኝ፡፡ አይኖቼን ጨፍኜ ያመንኳቸው ሰዎች ተጨንቄ ስገልጣቸው አልነበሩም፡፡” እያለ የስደትን ከባድነት ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ወጣቶቹ ባለማገገናዘብ የሚነገራቸውን ሁሉ ያምኑ እንደነበር ይጠቁማል፡፡
ስለ አለም አቀፍ ፍቅር ያስተማሩኝ ያገሬ ምሁራን እንዳልሰለጠኑ… ጉያቸው ተደብቆ የሚያዛቸው ብርማ ከርፋፋነት እንደ ነበረ ገባኝ፡፡ ለሀገር በቀል ዕውቀት እና ፍልስፍና የነበረውን ዝቅተኛ አመለካከት ከፈረንጆቹ አምባ ካለው እውነት ጋር እያስተያየ መፀፀት ይጀምራል፡፡
ይኼኛው መንገድ የዓለሙ የስደትና የፀፀት ጐዳና ነው፡፡ አውቀንም ሆነ ተሳስተን፣ ወደንም ሆነ ተገደን ያደረግነው የፈፀምነው ነገር በአንዳች አጋጣሚ ስህተት ጣቢያ ላይ ሲጥለን ዘግይተንም ቢሆን እንፀፀታለን፡፡… ግን ፀፀቱ ሊተረምም ላይታረምም ይችላል፡፡ በዕድሜ፣ በጊዜ፣ በሁኔታዎች ይወሰናል፡፡ …. ግን ህሊናችን ይፀፀታል፡፡ እናም “ የልጅነቴን ሀጥያትና መተላለፍ አተስብብኝ “ እንዳለ ዳዊት በመዝሙሩ ሌላ የንስሀ መንገድ ይጀምራል፡፡
እግሩ በቻ ሳይሆን እግረ ህሊናው የኑሮ (ህይወት) ጐዳና ላይ የዛለ ተስፋ የማይታየው በእውነት ብቻ ሳይሆን በህልሙም ሀገሩ ጐዳና ላይ የሚንከለወስ ስደተኛ ሆኖ ይታያል፡፡ “ቤዛዊት እወደያ ስልክ ታናግራለች”፡፡ ይለንና ስለምን እንደምታወራ ግን አይገልፅም፡፡ ሁለቱም አንድ አልጋ ላይ ተቀምጠው አንድ ክፍል ውስጥ ሆነው በአይነ ህሊና ግን ወደ ምኞታቸው ወደ ህልም ዓለማቸው መንገዳቸውን ያንፀባርቃል፡፡
የሂስ ምርጫ
የእኔ የሂስ ምርጫ ስነ ማህበረሰባዊ ሲሆን ደራሲው በልቦለድ (በድርሰቱ) የማህበረሰቡን ገፅታዎች ምን ያህል አንፀባርቋል በኖረበት ዘመን የነበሩ ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴዎችና፣ ክንዋኔዎችስ በጥሩም ይሁን በመጥፎ እንዴት ገልፂቸዋል በስነ ፅሁፍ ስራው ውስጥስ በምን ያህል ተንፀባርቋል የሚሉት ነጥቦች ላይ ሂስ ማቅረብ ይሆናል፡፡
ደራሲ አዳም ረታ ‘ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ’ (የሰባት መንገዶች ወግ) ለሚል የፃፈው ልቦለድ “ መንገድ አይኑ ይፍሰስ አይባልም ደርሶ
የወሰደውን ሰው ያመጣል መልሶ”
በሚለው የባህል ዘፈን ስንኝ ሲጀምረው መንገድ አይኑ ይፍሰስ የሚለው አገላለፅ መንገድ አይን እንዳለው እንድናስብ አያደርገንም፤ ዳሩ ግን በሰውኛ ዘይቤ አንድ ሰው ‘አይኑ ይፍሰስ’ ከተባለ ይሙት፣ ይጥፋ፣ የሚል ትርጓሜ እንዳለው በዘልማድ ስለምናውቅ የማህበረሰቡ ብሂል ነውና እርግማን መሆኑን እንረዳለን፣ እናም መንገዱ የሄደበት የሚመለስበት ጐዳና ነው፡፡ በመሆኑም ስንለያይ መንገድናን ብንረግመው የሄደው መመለሻ እንዳያጣ ነው፡፡ ይኼው ቁርኝት እንዳይበጠስ የሚያደረግ አስተዋፅዖ እንዳለው አመልካች ነው፡፡ ምንም እንኳ ስንኞቹ የደራሱው ፈጠራ ባይሆኑም፤ የተጠቀመው ግን አንዳች ፋይዳ ቢኖራቸው ነው፡፡
ሰባቱን መንገዶች ከጥቃቅን የአቧራ ብናኞች ጀምሮ፣ የምንጓዝበት መንገድ፣ ወደዚህች አለም የመጣበትን መንገድ፣ ድክ ድክ ያለበትን፣ በዕውቀት፣ የጐለመሰበትን የዕውቀት መንገድ፣ ከትምህርት አፈንግጦ ግራ የተጋባበትን የፖለቲካ መንገድ፣ የተሳሳተበትንና፣ ጥፋት የፈፀመበትን መንገድ፣ ከሀገሩ ተሰድዶ የወጣበትን መንገድ፣ በስደት በናፍቆት የተመላለሰበትን የሀሳብ መንገድ፣ እውነታውን ከሀሰቱ የለየበት የግንዛቤ መንገድ፣ በፀፀት ትናንትን እየናፈቀ ዛሬውን የሚኮንንበት እንዲሁም በህይወት ስላለ ስለ ነገው መንገዱ ንስሀ የሚባበት ከግዑዙ የምድር ላይ መንገድ እስከ ምናባዊው የአይን ህሊና መንገድ በጥልቀት ይተርካል በሰባቱም መነግዶች መካከል ጥብቅ ቁርኝት ያለና አንዱ ለአንዱ መሠረት መሆኑን በታሪኩ የፍሰት ቅድም ተከተል እንዳይጎረብጥ ሆኖ ቀርቧል መንገዱ ሲጠናቀቅም “ ይኼኛው መንገድ ያለፈውን አይሽርም” እያለ ቁርኝታቸውን ይበለጥ አፅንዖት ይሰጣቸዋል፡፡
የደራሲው ፍጡር የሆነ ገፀ ሰብ ዓለሙ አንዲን መንገዱን ሲያጠናቅቅ የሚጠቀማቸው መፅሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ያለውን የግዕዝ ቋንቋ ሲሆን፣ ይኸውም ከመንገዱ መጀመሪያ
…. ይሄ መንገድ…. አይሽርም “ ከሚለው አገላለፅ ጀምሮ ከቤተ ክርስቱያንቱ አስተምሮ ውስጥ ስለ ስላሴ አንድነትና ሦስትነት የሚገልፀው ክፍል ላይ
…. አብ አባት ስለሆነ ከወልድ አይበልጥም
ወልድም ልጅ ስለሆነ ከመንፈቅ ቅዱስ አይበልጥም
መንፈስ ቅዱስም ትክክል ነው፡፡ “ ከሚለው አገላለፅ የተቀዳ ነው፡፡ ሌሎችም ለዚሁ ማሳያ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ለምሳሌ (111) ወቅቱ የመር ወቅት መሆኑን ለመንገር
አሠርገወ ሰማየ በክዋክብት
ወለ ምድርኒ አሠርዋ በፅጌያት/ ሰማዩን በከዋክብት ሸፍነውታል ምድርንም በአበቦች አባምሯታል (ቅዱስ ያሬድ የገጠመውና ያዜመው)
ለሞቱ ሰዎች የሚደረግ ፀሎት የሆነውን (124)
ፀልዩ በእንተ እለ ኖሙ / ለአቀላፉት ፀልዩ
“ ሞተ ዘኢይመውት” / የማይሞት እሱ ሞተ
መንገዱን በፀፀት ተጉዞ ራሱን በንስሀ ሲያዘጋጅም
“ሃጢያትይ ዘበእንስየ ወእበድየ ኢትዘክር ሊተ”
የልጅነቴን ሐጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ (መ.ዳዊት 24.7)
ከዚህ ማየት የሚቻለው ደራሲው ጠለቀ የሐይማኖት ዕውቀት ያለው በሌላ በኩል ደገሞ የመጠቀ የቋንቋ እውቀትና የድርሰት ችሎታ እንዳለው ነው፡፡
የወቅቱን ፖለቲካዊ ኩነት በጥንቃቄና ምስል ከሳች በሆነ አገላለፃ ማቅረቡ የነበረውን ጥልቅ መረዳትና የወቅቱ እንቅስቃሴ አካል እንደነበረ ያሳያል፡፡
ይኼንን እውነት በዚሁ የልቦለድ መድብል ውስጥ “የመንግስቱ ነዋይ ጊዜ” በሚለው ድርሰቱም በዝርዝር የነበረውን ሁኔታ በተባ ብዕሩ ደግሞ ፅፎታል፡፡
ደራሲው የራሱን ፍጥር ቃላት አስፈላጊ ናቸው ብሎ ባመናባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ የሚጠቀም ትርጓሜያቸውም ለአንባቢ ሩቅ እንዳይሆን ተጠንቅቀቆ የሚፅፍ ሲሆን ለምሳሌ (1ዐ1) ያንቸለቸልኩት የሚለው ቃል የተጠቀመው ለንባብ ስለሆነና በጣም ጉብዝናውን ለመግለፅ ስለበር በተለምዶ/ ያንበለብለዋል፣ አንበለበለው/ ሳይደነቃቀፍ አንበበው የሚለው ትርጉሙ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ያስችላል፡፡
በቋንቋ አጠቃቀሙ የኖረበትን ዘመን በጥልቀት መግለፅ የቻለ፣ የራሱ የሆነ የተለየ የአፃፃፈ ስልት በተለይም አጫጫር ዐ.ነገሮች የሚጠቀም ሲሆን ግጥም የሚመስሉ የቅርፅ ይዘት ያላቸውም አሉ፡፡
ደራሲው ንግርትን እንደ አንድ የመተረኪያ ዘዴ ተጠቅሟል
(94) “በወፍ መበተን ምሳሌ ፍቅር ማፍረስን አለማምዶኛል”
ዓለሙ ካደ በኋላ ፖለቲካ ገባኝ ባለት የጉርምስና ዘመን አብሮ አደግ ጓደኛውን ሳራን ባንዳ ናት ብሎ ለገዳይ አሳልፎ ሰጥቷታል፡፡ (118)
(1ዐዐ) ስለማይገባኝ ነገር እንደ ገባኝ ሁሉ መዋሸት እዚህ ተምሬያለሁ ዓለሙ ያልገባው ፖለቲካ እንደ ገባው የዋሸበትን ዘመን “…. ዓይኖቼን ጨፍኜ ያመንኳቸው ሰዎች ተጨንቄ ሳገልጣቸው አልነበሩም፡፡ (1994) ይላቸዋል፡፡
ህልም (1ዐ8)….. እሷ ዋርካ ስር አህዮች፣ በቅሎዎች፣ ግመሎችና ሰዎች ከዝናብ ተጠልለዋል፡፡ እሳት ከዋርካዋ ስር ይነዳል፡፡
እንደ ዋርካ ለሁሉ መጠለያ የነበረችው ሀገር እሳት ሲነድባት ፓለቲካ እሳት ሆኖ ልጆቿን ሲፈጅ ቆይተን እናያለን፡፡
ደራሲው የራሱን ፈልስፍናም አንፀባርቋል፡ (111-112) አንዳንዴ ተጠናቅቆ ያልደረቀ አሳቻ ቦታ ጨፍርር ያለ ሳር ስር በጥቢኛ እግሬ ማህተም ሳደርግ ተመልሶ ስፈልጋት ትጠፋብኛለች…. ቦታው ሲጠፋኝ አላገኘኋትም እንጂ አልጠፋችም በሚል ራሴን አፅናናለሁ፡፡
መጀመሪያ ስፈልጋት ትጠፋብኛለች “ ካለ በኋላ” …. ቦታው ሲጠፋኝ” ይላል፡፡ ተፈልጎ የጠፋ ነገር ጠፋ ነው የሚባለው፡፡ ቀጥሎ ግን ቦታው ሲጠፋኝ ይለየናል፤ ይህ ማለት ያኖረበት ቦታ እንጂ የጠፋው ያኖረው ነገር አለመጥፋቱን ይነግረናል፡፡ ስለዚህም “ አላገኘኋትም እንጂ አልጠፋችም “ ሲል ድምዳሜ ይሰጣል፡፡ በሌላ ጐኑ ስናየው ይቼ ፍልስፍና እውነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይሄውም አንድን ዕቃ ወይም አንድን ነገር አስቀምጠን ፈልገን ካጣነው የፈለግነው ያላስቀመጥነበት ቦታ ላይ ነበር ማለት ነው፡፡
ደራሲው በዚህ ድርሰቱ ርዕስነት በታተመው መፅሐፍ (መድብል) ውስጥ ስምንተ ሥራዎቹን አቅርቧል”፡ በሥራዎቹም የማህበረሰቡን (የሀገሪቱን) ታሪካዊ፣ ኢኰኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ሳይንሳዊ እውነታዎች ዘመኑ ላይ ሆኖ አሳማኝ በሆነ እውነት ላይ ተመርኩዞ በበሰል ቃላት መስል ከሳች በሆነ መልኩ የቀረበ ለሀገራችን ስነ ፅሁፍም የራሱን አሻራ የተወ ሥራ ነው፡፡
ሙላትና ክፍተት
ሙላት
ደራሲ አዳም ረታ በይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ ልቦለድ ውስጥ ከቃላት አጠቃቀምና ምርጫ ጀምሮ ማህበረሰቡን በዘመኑ ላይ በደንብ መግለፅ የቻሉ በጥልቀት ስዕልን በአንባቢ አዕምሮ ውስጥ ማኖር የሚችሉ ትውስታዎችን የማቆየት አቅም ያላቸው የዐ.ነገር አስካክ ተጠቅሞ ይህንን ትልቅ የሥነ ፅሁፍ ሥራ ለህዝቡ በማቅረቡ ያለኝ አክብሮትና አድናቆት ከፍ ያለ
ክፍተት
ደራሲ አዳም ረታ የራሱ አፃፃፍ ስነ ዘዴ ያለው መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ ልቦለድ ውስጥ እንደ ክፍተት የታየኝ ተራኪው ከልጅነት ጀምሮ ያለውን ህይወቱን ሲተርክ በመሀከል ወደ አሁኑ ዕድሜው እየገባ እየወጣ ስለሚተርክ ለጀማሪ አንባቢ ግራ የሚያጋባ ሆኖ ተሰምቶኛል፡፡
እኔ እንደ ጀማሪ ሃያሲ የታየኝን እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡፡ በዚህ ሃሳብ ላይ የምትሰጡኝን ማንኛውንም አስተያየትና ተጨማሪ ሂስ ለመስማት ዝግጅ መሆኔን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

13/02/2019

COLLAGE OF PERFORMING & VISUAL ART SCHOOL OF THEATER ART
ASSIGNMENT on criticism

ሳምራዊት ሐድሽ

“ዕንቁጤ - ዕንቁጣጣሽ”
እና
ሌሎች ልቦለዶች

በረዳት ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ

1. መግቢያ አንቀጽ (ዳራዊ ሐተታ)
“ዕንቁጤ እንቁጣጣሽ” የተሰኘው አጫጭር ልቦለዶችን የያዘ ሲሆን ለማንበብ አጓጊ እና በውስጡም የተለያዩ ማህበረሰባችንን እያስተማረ እና እያዝናና በማህበረሰቡ ውስጥ ገብቶ የማህበረሰቡ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸውን ይዞ በማህበረሰቡን ወክለው የተሳሉ ገጸ-ባህርያት እና ህብረተሰቡን አዝናኝና አስተማሪ የሆነ አጫጭር ልቦለዶች የያዘ መጽሀፍ ነው። በማህበረሰቡ ትኩረቱን ያደረገ ይህን እንቁጤ እንቁጣጣሽ የተሰኘው በማህበረሰባችን የሚያጋጥመው የፍቅር የሀዘን ውጣ ውረድና የማህበረሰቡ አኗኗር ፣ የትዳር ውጣ ውረድ፣ በቀል ፣ ሙስና ፣ የህይወት ፈተናዎች፣ ችግሮች እና የተለያዩ ውጣ ውረዶች በማህበረሰቡ የሚያሳይ የአጫጭር ልቦለዶችን የያዘ መጽሀፍ ነው።

2.የስራው ገለጻ
ታህሳስ 2000 ዓ.ም የታተመው “እንቁጤ እንቁጣጣሽ” እና ሌሎች ልቦለዶች
የተሰኘው መጽሀፍ በረዳት ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ የተጻፈ የውጭ ሽፋን ፎቶግራፍ ደግሞ በስማቸው ዳኘው የተሰራ አጫጭር ልቦለዶችን የያዘ መጽሀፍ ሲሆን አትኩረት አድርጎ የተጻፈው ደግሞ በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ያለውን የፍቅር፣የሀዘን፣የሙስና፣ስስት እና የተለያዩ በኢትዮጵያ ማህበረሰብ የሚያጋጥመው ገጠመኞች ሁሉ አስተማሪ ነው ብሎ የታሰብ ሁሉ ተካተውበት እናገኘዋለን።በአጠቃላይ በሀገራችን ውስጥ ያለውን የኑሮ ዘይቤ እና የአኗኗር ስርዓቶች ባህል ተደርጎ የተጻፈ ነው።

3.ምስጋና

ረዳት ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ ለሀገራችን ብዙ ስራዎች ያበረከተ ሲሆን ከነዚህም መካከል ተውኔት (በትርጉም ስራ)፣ የህጻናት ተውኔት ፣ የዓዋቂዎች ተውኔት ፣ ጥናታዊ እና አጫጭር ልቦለዶች ስላበረክትክልን ስላቀረበልን ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

4. የስነ ሂስ ምርጫ
የስነ ሂስ ምርጫዬ ያደረግኩት ማህበራዊ ስነ ሂስ ሲሆን ይህ ማለት የቻልኩት ደግሞ እንቁጤ እንቁጣጣሽ ጨምሮ በውስጡ ያሉትን አጫጭር ልቦለዶች ገና ከመነሻቸው ስንመለከታቸው በማህበረሰቡ ያለው ግኑኝነት አትኩረታቸውን ስለሚያደርጉ ነው። የማህበረሰቡ ገጽታዎች በጽሁፉ ላይ አንጸባርቀው እንመለከታቸዋለን።ምክንያቱም መጽሀፉ የተጻፈበት ዘመን እና ውስጡ ያሉትን ጽሁፎች ማህበረሰቡ ይኖርበት የነበረው የአኗኗር ጊዜ ስለነበረ አንድ ሊያደርገው ችሏል።

5.መነጻጸሪያ ቀደምት ስራ እና አስረጅነት
ደራሲው ረዳት ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ስም ካላቸው ደራሲያን አንዱ ነው። ረዳት ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ ከሰራዎች ስራዎች መካከል የትርጉም ስራ፣ የህጻናት ተውኔት፣የአዋቂዎች ተውኔት ፣ አጫጭር ልቦለዶች እና ጥናታዊ ጽሁፍ የጻፈና ያዘጋጀ ሲሆን የሰራቸው ስራዎች በዝርዝር ስናያቸው ደግሞ፦

1. የተውኔት ትርጉም ስራ
 በ1981 “ቅኝት” የተሰኘ ቴአትር በማክሲም ጎርኪ ተደርሶ በረዳት ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ ተተርጉሞ በበሀይሉ መንገሻ አዘጋጅነት በብሔራዊ ቴአትር የቀረበ ስራ ነው።
“ከእንቁጤ እንቁጣጣሽ” ስራው ቀድመው ለህትመት የበቁ ስራዎች ስንመለከት ደግሞ፦
2. የህጻናት ተውኔት
 ኩኩ መለኮቱ
 የሰማዩ ሰረገላ
 አባ ጉጉ

3. የዓዋቂዎች ተውኔት
 ሊቀ-ማዕምር
 ኩረባ

4. ጥናታዊ
 ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በጥንታዊ ግሪኮች እሳቤ

5. አጫጭር ልቦለዶች
 ታህሳስ 2000 ዓ.ም የታተመው “እንቁጤ እንቁጣጣሽ” እና ሌሎች ልቦለዶች

6. ከስራው አስርጂነት
“እንቁጤ እንቁጣጣሽ” እና ሌሎች ልቦለዶች የውስጥ ይዞታቸው ስንመለከት በኢትዮጵያ ማህበረስብ ያተኮሩ እና ባህላቸው እና ወጋቸውን ጠንቅቀው የተሰሩ ናቸው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንቁጤ እንቁጣጣሽን ጨምሮ ወደ አስር (10) አጫጭር ልቦለዶችን ይዞ እናገኘዋለን። እነሱም፦
1. እንቁጤ እንቁጣጣሽ
2. እልሀኛው
3. ብሩ ብልቢሌ
4. ዥዋዥዌ
5. በቀል
6. ድግግፎሽ
7. ዲቪ ያገኘችዋ
8. የእሙቲ ሥዕል
9. ቦሎ ከላውዶ
10. ውጤት ናቸው።
እነዚህ ወደ አስር (10) የሚሆኑ አጫጭር ልቦለዶች የየራሳቸው የሚያስተላልፉት መልዕክት አላቸው። በሌላ በኩልም የሚያስተላልፉት መልዕክት ተመሳሳይነት ያላቸውም አሉ። መልዕክታቸው ሰውን እያዝናኑ ግን በጣም በሰው ልጅ ህይወት አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉ መልዕክት ሁሉ ያስተላልፋል። ከነዚህ አስር አጫጭር ልቦለዶች ሁለት የተለያዩ አጫጭር ልቦለዶች አንድ ዓይነት መልዕክት ሲያስተላልፉልን ሌሎች ሁለት አጫጭር ልቦለዶች ደግሞ ተመሳሳይ መልዕክት ያስተላፉልናል። ከሚያስተልፉልን መካከል፦
1. እንቁጤ እንቁጣጣሽ
2. ድግግፎሽ
እነዚህ ሁለቱ ዓብይ ርዕሰ ጉዳያቸው የሚያደርጉት “ፍቅር” ነው።
1. ዲቪ ያገኘችዋ
2. ቦሎ ከላውዶ
እነዚህ ደግሞ ተመሳሳይ መልዕክት የሚያስተላልፉልን ሆነው ዓብይ ርዕሰ ጉዳያቸው የሚያደርጉት “ሙስና” ነው።

እንቁጤ እንቁጣጣሽ፦ ስንመለከተው በተለያየ መልኩ ደራሲው በዚህም ስራ ብቻ አይደለም በሁሉም በዚህ መጽሀፍ ያሉት አጫጭር ልቦለዶችን ተምሳሌታዊ (symbolic) በሆኑ ነገሮችን አድርጎ ሲተርክልን እንመለከተዋለን። እዚህ እንቁጤ እንቁጣጣሽ ላይ ነጠላ ውጤት ነው የምናየው። በዚህም የአጭር ልቦለድ አስፈላጊውን ነገሩ አሟልቶ እናገኘዋለን።በተምሳሌት ስንመለከታቸው ደግሞ አብዛኛዎቹ ታሪኩን እንዲራመድና ጥድፊያ የተሞላው እንዲሆን ያደርገዋል ከእንቁጤ እንቁጣጣሽ ተምሳሌታዊ “ወለሉ ላይ ደግሞ ቅንብጣቸው የተለቀመላቸው የለዘዙ ቅጠሎች የካባ ቅጠል፣ የመኪና የውስጥ አካል፣ የእርሳስ ንድፍ፣ ክላሰር፣ የፔርሙስ ክዳን፣ ሱሪ፣ ካልሲ፣ ጫማ፣ የአልጋ ልብስ፣የስኳር ፍሳሽ፣ የቴፕ ክሮች፣ የሲጋራ ቁራጭ ተበታትኗል። ሲያያቸው መልሰው ያዩታል። አንደበታቸው ሳይከፍቱ በልባቸው “አንተ ብቸኛ---ሰነፍ!” እያሉ የሚያፈጡበት መስለው ከዓይናቸው ለመሸሽ መብራቱን አጠፋ። አንሶላውን ተከናንቦ ኩርምት ብሎ ተኛ።” ሲል እንመለከተዋለን ይህ ማለት ለሰለሞን ከብቸኝነት እንዲገላገል ምን ማድረግ እንዳለበት የሚገልጽ እና ታሪኩን እንዲራመድ የሚያደርግ ሲሆን ሰው በብቸኝነት መኖሩ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ያስረዳናል።
ድግግፎሽ፦ ስንመለከተው ደግሞ ከእንቁጤ እንቁጣጣሽ ተመሳሳይነት የፍቅር ርዕሰ ጉዳይ ያነሳ ሲሆን ነገር ግን ቦታው ከከተማ ወጣ ያለ በክፍለሀገር ውስጥ የተፈጸመው ታሪክ ነው የሚገልጽልን። ድግግፎሽ ላይ የምንመለከተው በሮይ ከተማ ያለውን የክረምት ድባብ እና የልምላሜ ደስ የሚል ነገር እናያለን። እንደ እንቁጤ እንቁጣጣሽ ልምላሜ እና የመጀመሪያ አፍቃሪ እንደ አዲስ ዘመን ወክሎ እናያለን።

ዲቪ ያገኘችዋ፦ ስንመለከተው ደግሞ ዓብይ ርዕሰ ጉዳዩን የሚያደርገ ሙስና ሲሆን በሙስና ትዳር ሲፈርስ እና ካለ አቻ ጋብቻም የሚታይበት እና በተጨማሪም በሙስና የብዙ ሰው ህይወት ሲመሰቃቀል እና እድላቸውን ሲፈርስ እንመለከታለን። ሙስና የሰራው ሰውየም በስስታምነቱ ለማይረባ ነገር ሲል ሳያረጋግጥ የገባውን ነገር ወደ አደጋ ሲጥለው እንመለከታለን።
ቦሎ ከላውዶ፦ ስንመለከተው ደግሞ ዓብይ ርዕሰ ጉዳዩን የሚያደርገው ልክ ዲቪ ያገኘችዋን ተመሳሳይነት በሙስና የተመለከተ ጉዳይ ሲሆን ነገር ግን ሙስና መስራት ያልፈለጉ ሀኪም በመስሪያ ቤቱ የሰዓት መግደልና ነገ ከነገ ወድያ ማለታቸው የሰልቻቸው ባለ ጉዳይ ሌላው እንደ እሳቸው ስላዩ እና እሱም ካልተሰጣቸው እንደማይሰሩ እና ሀኪሙ ካልሰጡ ጉዳዩ እንደማይሰራላቸው ሲነገራችው ያላቸው አማራጭ ሰው እንዳደረገ ማድረግ እንደሆነ ሲገባችው እና ጉቦ ለመስጠት ሲሉ ራሳቸው ጉድ እንደተሰሩ የሚያመላክት እና የሚያደርሰው ችግር እንመለከታለን።
ስራው ስንመለከተው አጫጭር ልቦለዶች ማሟላት ያለበትን አሟልቶ እናገኘዋለን።
7. ውሳኔ
1.ሙላት
የዚህ የእንቁጤ እንቁጣጣሽ እና ሌሎች አጫጭር ልቦለዶች ሙላቱ የምለው ልቦለዶቹ በዚህ በሀገራችን ማህበረስብ መሰራታቸው እና መሳጭ፣ሌላኛው ለማንበብ አጓጊ መሆኑን እና የቃላት ምርጭ እና ተምሳሌትን የሚሰጣቸው ለአንባቢ ክፍት እና ግልጽ ናቸው።

2.ክፍተት
ክፍተት ሆኖ የታየኝ የመጽሀፉ ርዕስ (እንቁጤ እንቁጣጣሽ) የተሰኘው ከውስጥ ይዘቱ ጋር አለመጣጣሙን ነው። በውስጡ ያሉትን ለየት ያሉና ትምህርት ሰጪ እንደመሆናቸው መጠን እንደ ውጫዊ ክፍሉ ቀለል ተደርገው የሚታዩት አይደልም። በሽፋኑ ያለውን ርዕስ እና ምስል ስንመለከተው ቀለል ያለ ይመስለኛል። ነገር ግን ውስጡ ያለውን መሳጭና ቁም ነገር ያለው ስለሆነ ሊጋጭ ይችላል ባይ ነኝ።

8. መደምደምያ ሀሳብ
እንቁጤ እንቁጣጣሽ ስታነበው የሚያጓጓና እያዝናና የሚያስተምር ስለሆነ ረዳት ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። ውስጥ ገብተን ጠለቅ ብለን ብናነበው ብዙ ልምድና ዕውቀት የምንገበይበት ነው እላለሁኝ። የውጭ የሽፋኑ ርዕስ እና የውስጥ ይዘቱን ስለሚለያይ ግን እንደነዚህ ውስጣቸውን ማራኪ የሆኑ ታሪኮች ሲጻፉ ርዕሳቸው ወሳንነት ስላለው ትኩረት ተሰጧቸው መስራት አለባቸው እላለሁኝ።

9.ክፍት ትህትናዊ አጨራረስ
እንቁጤ እንቁጣጣሽ የተሰኘው አጫጭር ልቦለዶች መሰራቱን በጣም አደንቃለው። ክፍተቱን የምለው ውጫዊ ሽፋኑን ሲሆን ግልጽ በሆነ ርዕስ ቢሰራ እና ከርዕሰ ጉዳዩ ገላጭ ቢሆን እላለሁንኝ። ሌላ ሰው ደግሞ እንደ እኔ አንብቦ የራሱ የሆነ ሂስ እንዲሰጥ እላለሁኝ። አመሰግናለሁ።

13/02/2019

የስነ ጥበባት ኮሌጅ
የትያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል

ከጥቁር ሠማይ ስር በተሰኘ አጫጭር ልቦለድ ከያዘው መፅሀፍ ከስነ ማህበራዊ ሂስ እይታ

ለ Critics ኮርስ ማሟያ የቀረበ

በ የምስራች አባትሁን

የካቲት 2011
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
ምስጋና
በዚህ ስራ የረዳኝን ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ፡፡ በመቀጠል ከማያልቀው የእውቀት ባህሩ ስንት አመት እየጠለቀ ሲያጠጣኝ የኖረውን መምህሬን ጳውሎስ አዕምሮን አመሰግናለሁ፡፡ እጂን ቁርጥማት እንኳን እንዳይነካው የምመኝለት ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደን ስራዎቹን ለአንባቢ በማብቃቱ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ እንዳለጌታ ከበደ ከእውቀቱ ባሻገር ቅንነቱ የሚገርም ነው ምንም ሳያመላልሰኝ በአንድ የስልክ ጥሪ ለሰጠኝ መረጃ እግዚአብሔር ያክብርልኝ ከእውቀትህ በጤና ያቆይህ እላለሁ፡፡

ቅርፃዊ ይዘቱ
• ዘመናዊ አጭር ልቦለድ ፈጣሪ “Edgar Allen Poe” ይባላል፡፡ ይህ ሰው የዘመናዊ አጭር ልቦለድ ደራሲ ብቻ አይደለም ገጣሚም ጭምር ነው፡፡ “Edgar” ስነ ውበታዊ አቀንቃኝም ነው፡፡
• የአጭር ልቦለድ ባህሪያት ብለን የምናነሳቸው መሰረታዊ ጉዳዮች፤ ቁጥብነት፣ ጥድፊያና ነጠላ ውጤት ናቸው፡፡
አጭር ልቦለድ የምንጠቀማቸውን ቃላት የተቆጠበና የተመጠነ መሆን አለበት፡፡ በአጭር ልቦለድ ህግ ታሪኩ ቶሎ ቶሎ እየፈጠነ ሄዶ ወደ ፍፃሜ መድረስ አለበት ስለዚህ ጥድፊያ ሊኖረው ይገባል፡፡ ጥድፊያው ወደ አንድ ነጠላ ውጤት ያመራናል፡፡


የደራሲው የህይወት ታሪክ
እንዳለገታ ከበደ ወልቂጤ ከተማ ተወለደ 1ኛና 2ተኛ ደረጃ ትምህርቱንም እዛው ተምሮ አጠናቋል፡፡ አዲስ አበባ መጥቶ ዩኒቲ በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በጊዜጠኝነትና በኮሚኒኬሽን ትምህርት ዲፕሎማውን ያዘ፡፡ ከዛ በ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቴአትር ጥበባት ት/ክፍል በማታው መርሃ ግብር ዲግሪውን ይዟል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪው ደግሞ በኢትዮጵያ ስነ- ፅሁፍና ፎክሎር የያዘ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ሶስተኛ ዲግሪው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፎክሎር እየተከታተለ ይገኛል፡፡
እንዳለጌታ ከበደ ዩኒቲ ዩንቨርስቲ ኮሌጅ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ባልደረባ እና የባህል ማዕከል ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በዋና ፀሀፊነት በብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ስላሴ የስነ ጥበብ ማዕከል (የኢትዮጵ ሳይንስ አካዳሚ ባህል ማዕከል ዳይሬክተር ነው፡፡
የመፅሀፍ አበርክቶው ከጥቁር ሰይማ ስር የመጀመሪያ ስራው ሲሆን በመቀጠል ዛጎል፣ የመኝታ ቤት ሚስጥሮች፣ ኪርሻዶ፣ ልብ ሲበርደው፣ ደርሶ መልስ፣ ፅላሎት፣ እምቢታ፣ ማዕቀብ፣ በአሉ ግርማ ህወቱና ስራዎቹ (ታሪክ)፣ ያልተቀበልናቸው ስራዎች ባለቤት ነው፡፡ እነዚህ እጫጭር ልቦለዶች ረጅምና ኢ ልቦለድ ስራዎች እና የግጥም መፅሃፍቶች ናቸው፡፡ የመኝታ ቤት ሚስጥሮችና ፅላሎት እና ከጥቁር ሠማይ አጭር ልቦለዶች ናቸው ይሉኝታ የተሰኘ ፊልም ከቢኒያም ወርቁ ጋር በጋራ በፅሁፍ ስራ ላይ ተሣትፏል፡፡
ምጣዱ
ቀርነቱ
ደራሲው ከዋናው ታሪክ ጋር አብረው ሊጓዙ ይችላሉ ብሎ ያነሳቸው ጉዳዩ አንዱ ከሴተኛ አዳሪዋ ጋር /ከባለ ታሪኳ) ጋር የመጣው ባለ ትዳር አንቺ ጋር ለምን እንደመጣሁ ታውቂያለሽ ብሎ የመጣበትን ምክንያት ሲነግራት ምክንያቱ ለሷም ሆነ ለሱ አሣማኝ ሊሆን ይችላል ካሉበት ሁኔታ አንፃር ለአንባቢ ግን ምክንያቱ ተአማኒነትን እንዳያገኝ ውሃ የሚያነሳ ሃሳብ እንዳይኖረው አድርጎብኛል፡፡ ማህበረሰባችን እናትን አይደለም አንድ እግር የጣለው እንግዳ ቤቱ ቢመጣ እንግድነቱን ጨርሶ እስኪሄድ ድረስ ከበሬታው እንዳለ ነው፡፡ መኝታውን እስከመልቀቅም ይደርሳልና ይህም ገፀ ባህሪ ለሴተኛ አዳሪዋ ከሚስቱ ውጪ የሄደበትን የሚሰቱ እናት ቤታቸው መምጣታቸውን ሲነግራት ምክንያቱ ከባህል አንፃር አሳፋሪ ነው፡፡ ደራሲው ከሚስቱ ውጪ እንዲማግጥ ያደርገውን ምክንያት የልጁን ባለጌነት በሌላ መንገድ ቢገልፀው የተሻለ ነበር፡፡ ምክንያቱ አሳማኝ አልሆነልኝም፡፡
ደብዳቤዎቹ
ሙልአቱ
በኛ ማህበረሰብ ከተማም ሆነ ገጠር አንዲት ያለገባች ሴት በተለይ ደግሞ ታናናሾቿ ትዳር የያዙና ጎጆ የመሰረቱ አልፎም የወለዱ ከሆነ፤ ማህበረሰቡ እንደኒጲኤል አይነቷን ያላገባች ሴት ምን ሊላት እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ ደራሲው አንድ ያላገባችን ሴት ስሜቷ ምን ሊሆን እንደሚችል በዚህ ደረጃ ተረድቶትና ገብቶት እንደዚህ አይነት ሃሳብ እንደምታስብ አውቆ መፃፉ ብቃቱን እንዳደንቀው አስገድዶኛል፡፡ በዚህ አጭር ልቦለድ ውሰጥ ዋናው ባለታሪኮች ሁለቱ ገፀ ባህሪያት ቢሆኑም በሴቷ ገፀ ባህሪ አማካኝነት ግን ማህበረሰቡን ቁልጭ አድርጎ አሳይቶኛል፡፡ ከወንዱ (ከናኦድ) ስሜት በላይ የሴቷ የኒጲኤል ስሜት እጅግ ገላጭ ነበር፡፡
የደራሲው ችሎታ የሚገርም ነው ወንድ ሆኖ ልክ እንደ ሴት የሴትን ውስጣዊ ስሜቷን በጥልቀት መረዳቱና ባማረ ሁኔታ መግለፁ ችሎታውን ያመለክታል፡፡
ሲጨልም
- ይህ አጭር ልቦለድ ማህበረሰቡ በቁም ከመረዳዳት ይልቅ ለሞተ ሰው ያለውን እርህራሄና ደግነት ነው የሚያሳየው፡፡ በዚህ ልቦለድ ከገፀ ባህሪያቱ አንዱ የሆነው ፋርማሲስቱ (መድሃኒት ሻጩ) ደራሲው ማህበረሰቡን ለማስተማሪያነት ቢጠቀመው መልካም ነበር፡፡ ለምሳሌ ባለ ታሪኩን (ሽማግሌውን) ከማንጓጠጥና ከማሽቆጥቆጥ ይልቅ መድሃኒቱ የማይመለስበትን ምክንያት በቅንነትና ሙያዊ ስነ ምግባር በታከለበት መልኩ ቢያስረዳቸው መልካም ነበር፡፡ ይህንን ልል የቻልኩበት ደራሲው ማህበረሰቡን ይወክላሉ ብሎ ያስቀመጣቸው ገፀ ባህሪያት ሁሉንም ለሙት አዛኝ እንዲሆኑ አድርጎ ነው የሳላቸው ቢያንስ አንዳቸውን ለቆመ (ላልሞተ) ማዘን፣ ማሰብ፣ መርዳት የሚችሉ ማድረግ ነበረበት፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ሁሉም እንደዛ አይደሉም፡፡ ሁሉንም ገፀ ባህሪ ለሙት አዛኝ ነው ለሙት ፈጥኖ ደራሽ ነው ብሎ ደራሲው መፈረጁ ቀርነቱን አጎልቶብኛል፡፡
ክፍተት
የዚህ አጭር ልቦለድ ቀርነቱ አንድ ተከራይቶ የሚኖር ወንደ ላጤ ከማህበረሰቡ ወይም ከአካባቢው ሰው ጋር ያለው መስተጋብር በአብዛኛው የላላ ነው፡፡ ብዙ አመታትን በዛ አካባቢ ሲኖርም እንኳን ከሰላምታ የዘለለ ውለታ እስከመዋዋል ይደርሳል ለማለት ይከብዳል በዚህ ልቦለድ ውስጥ ያለው የዘርፌ ባለቤትም፡፡ ደራሲው ለናቷ የዋለላቸውን ውለታ ቢኖርም ታሪክ ላይ መጨመሩ ግልፅ አይደለም ለዋናው ታሪክም ጥንካሬም ሆነ ግብአት ሲሆን አላስተዋልኩም፡፡ ለመጋባታቸው ከጎረቤት ተከራይቶ ይኖር የነበረው ወንደላጤ የሱ እናድትሆን ተመኘ ተሸነፈላት ለመገባታቸው ይህ በቂ ነወ፤፤ በዚህ አጭር ልቦለድ ውስጥ እንደ እትዬ ሻሼ አይነት እወደድ ባይ ጎረቤት፣ ከአሰሪው ጋር ችግርን ተጋርታ የምትኖር ሰራተኛ፣ ቤቱ ሲዘርፍ የማይበሳጭ አባወራ በየአካባቢያችን መኖራቸውን ደራሲው ቁልጭ አድርጎ አሳይቶኛል፡፡ ቀርነት አለው የምለው ነገር ቢኖር ሰራተኛዋ ጥፋተኛ እንዳልሆነች እያወቀች ቅጣቷን እንድትቀበል ያደረገችበት የዘርፌ ዝምታ ምክንያት አልባ በመሆኑ ቀረነቱን ያሳየኛል፡፡
በሰንበት የተፀነሰው
የስድስት ዓመቱ አቦቸር ቅልጥፍጥፍ ያለው አንደበቱ ብልጥ ቢያስመስሉትም ልጅነቱ ግን የማይካድ እውነታ ነው፡፡ በዚህ አጭር ልቦለድ ውስጥ ጥሩ ነገር የበዛ ቢሆንም ደራሲው ልብ ባላለት ጉዳይ ግን ቀርነት እንዲኖረው አድርጎብኛል፡፡ ምንትዋብ እስከ ዛሬ አቦቸር የሚማርበትንና አስተማሪውን የኔታን አለማወቋ ቀርነቱን ያሳየኛል፡፡ በአቦችር መሪነት ከቄሱ ትምህርት ቤት ሲደርሱ፤ የቄሱ መደንገጥ እሺ ይሆን ስለሚያውቋት ነው የምንትዋብ መደንገጥ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም አታውቃቸውማ፡፡ አቦቸርን ሊጠነስሱ የመጡበት ማታ ራሳቸውን ለውጠው ነውና ከምንትዋብ ጋር የዛሬ ስድስት አመት የተኙት፡፡

ማጠቃለያ
ከጥቁር ሰማይ ስር ከተሰኘው አጫጭር ልቦለዶች ከያዘው መፅሀፍ በተወሰነ አጭር ልቦለዶች ላይ በእኔ ሂሳዊ አተያይ ቀርነቱንና ሙላቱ ተመልክቻለሁ፡፡ ባቀረብኩት ስራ ላይ አስተያየት ካላችሁ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

12/02/2019

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
የሥነ-ጥበባት ኮሌጅ
የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት

እውነትን ስቀሏት በተሰኘው የግጥም መድብል ላይ የተዘጋጀ ሂሳዊ ዳሰሳ

ለCritics ኮርስ ማሟያነት የተሰናዳ

በ፡-
አብረሃም ታደሰ

የካቲት 2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
እነሆ ለCritics ኮርስ ማሟያ የሰራነው "ባዶ እግር" የተሰኘ ተውኔት ሲሆን አንብባችሁ ገንቢ አስተያየት እንደምትሰጡኝ በማመን ለእናንተ አጋርቻለሁ፡፡ መልካም ንባብ!
መግቢያ
የግጥሙ ደራሲ ሰለሞን ሞገስ ሲሆን ገጣሚ ሶስት የግጥም መጽሐፎችን ለተደራስያን ያበቃ ሲሆን እነሱም ጽሞና እና ጩኸት፣ ከፀሀይ በታች እና እውነትን ስቀላት የተሰኙት ናቸው፡፡ እነዚህ መጽሐፎች ለሂሳዊ ዳሰሳ የመረጥኩት እውነትን ስቀላት የሚለውን መፅሀፍ ነው፡፡
እውነትን ስቀላት በ2008 ዓ.ም ገጽ 82 ብዛት ተሰድሮ በአሳታሚውም ኤርሞን ኤም ማተሚያ ቤት ታትሞ በ25 ብር የመሸጫ ዋጋ የቀረበ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን ህትመት ዋጋ በማሻቀቡ ተከትሎ እየተሸጠ ያለው በ50 ብር እና ከዚያም በላይ እየተሸጠ ይገኛል፡፡
የግጥሙ አብይ ትኩረት
ገጣሚው አብዛኛዎቹ ግጥሞች ትኩረታቸውን የሚያደርጉት በአሁኑ ትውልድ ላይ ያሉትን ብሶቶች በተለያየ መልኩ ይገልጻል፡፡
በግጥሙ የመጀመሪያ ግጥም በዚሁ ትውልድ ላይ ያለውን ብሶት በመግለጽ ነው የሚጀምረው፡፡ የግጥሙ ርዕስም አክሱምን አቃጥሉት ሲሆን ብሶት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የተጻፉ ሌሎቹም የበሰለ ምግብ፣ ኑ እና እንቃም እስቲ የዓለት ጥበብ፣ ፀሀዮቹ እኛነን፣ ኩራተኛው ትውልድ፣ ያላወቅነው ኮሌጅ፣ መንገዱን አገኘሁ የሚሉት ግጥሞች ይገኙበታል፡፡ ገጣሚው በትውልዱ ላይ ብቻ አይደለም ብሶቱን የገለፀው በግለሰብ ደረጃ ወርዶ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ላይ ጭምር ነው፡፡
ደራሲው በቋንቋ ረገድ ደረጃ ማንኛውም ሰው ከቀን ተቀን ጉሮው ውስጥ የሚጠቀምባቸው ቃላት ስለሆኑ ማንኛውም ሰዎች በቀላሉ መረዳት እንዲችሉ ሆኖ የቀረበ ነው፡፡

ማህበራዊ ሂስ
የገጣሚውን ብሶት እኔም ብጋራም ነገር ግን ትውልድ የቅብብሎሽ እንጂ አንድ ትውልድ ብቻውን ተሰርቶ የሚቀመጥ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን ተበላሽቷል የምንለው ትውልድ ካለፈው ትውልድ የተቀበለው የተሳሳተ አመለካከት አለ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የኢትዮጵያ የ86 ዓመታት፣ የፖለቲካ መዋቅር ብንመለከት የአፄ ኃይለሥላሴ ስርዓተ መንግስት ንጉሳዊ አስተዳደር ሲሆን መሰረቱም የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ያደረገ ነው፡፡ ቀጥሎ የመጣው መንግስት ደግሞ የሶሻሊዝምን ርዕዮት የሚከተል ሲሆን ማዕዘኑን ሃይማኖቱ ላይ ያደረገ ማህበረሰብ ይዞ ከራሺያ በተዋሰው ስርዓት ህዝቡን ለ17 ዓመት መርቷል፡፡ በቀጣይ መንግስት የሆነው ደግሞ ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ሆነ ይህም ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡ ይህም እንደሀገር መሰረቱ የተዛባ ትውልድ እንዲኖር ያደረገው ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ አሁን ላለው ችግር ሁሉ ይኼ ትውልድ ብቻ ተጠያቂ ሊሆን አይገባም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ችግሩን በመሰረታዊነት ከትንሹ እስከ ትልቁ የሚያውቀው ሲሆን ነገር ግን እንደ ገጣሚም ሆነ እንደ ግለሰብ እንዴት ከችግሩ እንደምንወጣ ፍንጭ መስጠት የሚጠበቅበት ይመስለኛል፡፡
ገጣሚው በግለሰብ ደረጃ የተቸው ደራሲ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር ነው፡፡ ትችቱም ከምንክያታዊነት ይልቅ ግብታዊነት ወይም ስሜታዊነት በደነብ ይነገራል፡ እንደሚታወቀው ደራሲ ስብሃት በኢትዮጵያ ስነጽሁፍ ታሪክ የራሱን አሻራ ካስቀመጠ ፀሃፊ አንደኛው ነው፡፡ ፀሀፊው ከሌሎች ፀሀፊዎች በተለየ በተለያየ የአጻጻፍ ዘዴ በመፃፍ ይታወቃል፡፡ በጊዜው የነበሩትን ታላላቅ ፀሃፊዎች እንኳን ብንመለከት በአሉ ግርማ፣ ሃዲስ አለማየሁ፣ ዶ/ር ከበደ ሚካኤል እና ሌሎቹንም ብንመለከት የሚጽፉበት የአጻጻፍ ስልት አንድ ነው፡፡ ያ ማለት የሁሉም ስራ ተመሳሳይ ነው ማለት ሳይሆን አንደኛውን ስራቸው የሚጽፉበት መንገድ ቀጣዩም ስራቸው ራሱ የአጻጻፍ ዘዴ ማለት ነው ለምሳሌ ያህል በእውነታዊነት የአጻጻፍ ዘዴ ውስጥ ነው፡፡ ስብሀት ግን በሶስት የአጻጻፍ ዘዴዎች ማለትም እውነታዊነት፣ ተፈጥሮአዊነት እና ገደብ የለሽነት ስልቶችን በመፃፍ ለተደራስያን ያበቃ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ ስነጽሁፍ ታሪክ የተለየ ቦታ እንዲኖር ያደርገዋል፡፡ ሌላው ስብሃት ገጣሚው እንደሚለው ስለሴስ ብቻ የፃፈ ደራሲም አይደለም፡፡ አምስት ስድስት ሰባት፣ እነሆ ጀግና፣ አጋፋሪ እንደሻው የፃፈ ፀሀፊ እንደመሆኑ በዚህ መንገድ ብቻ ሊታይ አይገባም እላለው፡፡
ሙላቱ
- ሃሳቡን ባልተንዛዛ እና ባጫጭር ስንኞች መግለጽ መቻሉ ሳቢ እንዲሆን አድርጎታል
- የሃሳቡ ፍሰት አስደሳች እና የማንበብ ፍላጎትን ያነሳሳል፡፡
- አብዛኛዎቹ ግጥሞች ሲነበቡ የራሳቸው ዜማ አላቸው፡፡
- ለግጥሞቹ የሚሰጣቸው ርዕሶች ሳቢና ተገቢ ናቸው፡፡
- የገፅ ማውጫ ላይ፣ የመፅሐፉን ዋጋ እና የታተመበትን ዓ.ም በግዕዝ ቋንቋ መጻፍ የግዕዝ ቋንቋን እንድናውቅ ያነሳሳናል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡
ክፍተቱ
- በግጥም ጭብጥ ደረጃ ትኩረት ያደረገው በአብዛኛው ብሶት ላይ ነው፡፡
- በዚህ ትውልድ ላይ ያለውን ተስፋ ቢነግረን ወይም መፍትሄውን በግጥሙ አማካኝነት ቢያስነብበን ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ማንፀሪያ
ገጣሚው ማህበረሰባዊ ትችቱን በተለያየ አይነት መልኩ አቅርቧል፡፡ የገጣሚውን እና የሌሎች ገጣሚዎችን ግጥሞች በአስረጂነት አቀርባለው፡፡ በመጀመሪያ ግጥም ላይ በመጨረሻዎቹ ስንኞች ላይ እንዲህ ይላል፡፡
አክሱም ፋሲል ግምቡን ማቃጠል ነው ጥሩ
በዘመናችን ላይ እንዳይመሰክሩ
የበሰለ ምግብ በሚል ግጥሙ ደግሞ ትውልዱ ክብር የሌለውና ስራ እንደማይወድ በደዚህ አይነት ስንኞች ገልፆታል፡፡
ክብሩን የቀደደ፣ እርቃኑን የወጣ
ይሄ የኖህ ዘመን ተመልሶ መጣ

ምንም ላለመድከም ምንም ላለማሰብ
እባክህ ላክልኝ የተሰራ መርከብ
ትውልዱ በአደንዛዥ ዕፆች እንደተነከረ ኑ እና አብረን እንቃም በሚለው ግጥሙ ውስጥ አስፍሯል፡፡
ስራ ምናባቱ እውቀት ስልጣኔ
የጥበብ መንገዱ በርጫ ነው ወገኔ
የደራሲው ሌላኛው ስራው የሆነውን ከፀሀይ በታች ላይ እንዲሁ ብሶቱን ይገልፃል፡፡
አወይ ለትውልዴ
በዚህ በሌባ አገር የጅቦች በሆነው
መቼስ ምን ይደረግ ጨዋ-ባለጌ ነው
በዚህ ግጥም ውስጥ ሌላ ደግሞ ትላንት እና ዛሬ በሚል ርዕስ አስፍሯል፡፡
ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ በታሪክም የታወቀ
አነበበና ተማረ አወቀና ተጠመቀ
ዛሬ ያ ሁሉ ቀረና የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ነው
ሳያነቡና ሳያውቁ ገብቶ ተጠምቆ መውጣት ነው
ወርቃማው ትውልዴ በሚለው ግጥሙ ትውልዱ በውጭ ሀገር አስተሳሰብ፣ አለባበስ እና ውጭ በማያያቸው ነገሮች ምን ያህል እንደተሳበ በግጥሙ ውስጥ በደንብ ያሳየናል፡፡
በአጠቃላይ ገጣሚ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች አማካኝነት አሁን ላይ ያለውን ትውልድ ላይ ያለውን ብሶቱን በግጥም አስፍሯል፡፡ ይሄን የሱን ብሶት ሌሎችም ገጣሚዎች አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል በግጥማቸው በተለያየ መልኩ ገልፀውታል ከነዚህም መካከል ገጣሚ ጌትነት እንየው እውቀትን ፍለጋ በሚል ግጥሙ ውስጥ ቅኔ ስደተኞች በሚል ርዕስ ውስጥ ትውልዱ ላይ ያለውን ብሶተን ይገልፃል፡፡
የእኛ የዛሬዎች
የሀበሻ ልጆች
በአዲሱ አለም ስርዓት፣ በጥበብ ተጠምቀን
በሆሊውድ ሙቪ
በእንግሊዝ እግር ኳስ ትንታኔ ረቀን
እያለ ይቀጥላል ይህ ግጥም ከሰለሞን ሞገስ ወርቃማው ትውልዴ ጋር ተመሳሳይነት ሀሳብ አላቸው፡፡
ሌላኛው ገጣሚና ደራሲ አሌክስ አብርሃም እናት፣ ፍቅር፣ ሐገር በሚለው የግጥሙ መድብል ውስጥ ከማበዴ በፊት በሚል ርዕስ እንዲህ ሲል ያስቀምጣል፡፡
አገር ጭንጫ ሆነች
ትውልድ የሙጃ አረም
እምነት ተበላሸ
ጠፋ የእውነት ቀለም
ሕዝብ ተማረረ
እያለ እሱም እንደሌሎቹ ገጣሚዎች እና እንደ ሰለሞን ሞገስ እሱም በትውልዱ መምከን ላይ የራሱን እይታ በግጥም ያስቀምጣል፡፡

ማጠቃለያ
በገጣሚ ሰለሞን ገብሬ የቀረበው እውነትን ስቀላት የተሰኘው የግጥም መድለል ስለፍቅር፣ ስለፈጣሪ፣ አስተሳሰብ እንዲሁም ባብዛኛው ስለአሁኑ ትውልድ ያለውን እሳቤ ቆንጆ በሆነ ያሰፈረ ሲሆን በቀጣይም መፍትሄ አዘል ግጥሞችን ጨምሮ ይመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡

12/02/2019

የሥነ-ጥበባት ኮሌጅ
የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት

በብሄራዊ ቴአትር በመድረክ ላይ በሚገኘው "ባዶ እግር" ተውኔት የፍልስፍና አተራረኩ ላይ የተዘጋጀ ሂሳዊ ዳሰሳ

ለCritics ኮርስ ማሟያነት የተሰናዳ
የቡድኑ አባላት፡-
1. አብረሃም ታደሰ
2. መገርሳ ኩማ
3. የምስራች አባትሁን
4. መስፍን ከበደ
የካቲት 2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
እንደ መግቢያ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር በቀዳማዊ ሀይለስላሴቴአትር ተብሎ የተመሰረተው በ1948 ዓ.ም ለንጉሱ 25ኛ ዓመት የንግስ በአል ማድመቂያነት ነዉ የሚለዉ ታሪክ ሁሉም የሚታወቀዉና የተለመደአባባል ቢሆንም አንዳንድሰነዶች እንደ ሚያሳዩት ግን የቴኣትር ቤቱ አመሰራረት ታሪክ ከዚህ የላቀ ተልዕኮ እንዳለዉ ለመገንዘብ ይቻላል.፡፡
ጥናታዊ ጹሁፎችና የታሪክ ሰነዶች አንደሚገልጹት በ1940ዎቹ መጀመርያ አመታት አካባቢ አንደ ፊልም መጽሄትየሸከላ ሙዚቃና ቴፕ በመሳሰሉ መገናኛ ብዙሃነ አማካይንት በምዕራበዊያን የባህል ተጽዕኖ እያደገ የመጣበት ጊዛ ሲሆን የሀገራችን ባህል እንዳይጠፋ ይሳሱ የነበሩ የኢትዮጵያ ምሁራን በአንድ በኩል ይህንን የባህል ወረራ ለመቋቋም በሌላ አቅጣጫ ደግሞከአለም ኪነጥብብ እድገት ለመቅሰም እንዲቻልየሀገራችንን የኪነጥበብ ዘርፎች መሰደግና ዘመናዊ ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን አምነዉበት ነበር፡፡
ከዚሁም ጋርየቀዳማዊ ኌይለሥላሴ መንግስት ብሄራዊ የሃገር ፍቅርና የጀግንነት ስሜትን ለማጠናከርና ፖለቲካዊ ማህወበራዊና ኢኮኖሚያው የሃገር ፋይዳ ያላቸዉን ቁም ነገሮች እያዝናኑ በህዝብ ዘንድ ለማስረጽሙዚቃናቴአትር ያላቸዉን ጉልበት እጅጉን ስላመኑበት የኢትዮጵያብሄራዊቴአትር ጥንስስ የሆነዉን የ

12/02/2019

ለስነ-ሂስ ኮርስ ሟሟያ ‹‹ የርዕሰ ጉዳይ አቀናቀንና የአዚያዚያም ስልት በበድሉ ዋቅጅራ ‹ የወይራ ስር ጸሎት › የግጥም መድብል›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን ይህንን ጹሁፍ አንብባችሁ ገንቢ አስተያየት ትሰጡኝ ዘንድ ለናንተ አጋራለሁ ፡፡
መልካም ንባብ
የርዕሰ ጉዳይ አቀናቀንና የአዚያዚያም ስልት በበድሉ ዋቅጅራ ‹‹ የወይራ ስር ጸሎት ›› የግጥም መድብል
ለስነ ሂስ ኮርስ ማሙያ የቀረበ

ቢንያም አያሌው
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
የስነጥበባት ትምህርት ቤት
የቴያአትር ጥበብ ትምህርተ ክፍል
የካቲት 2011 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ምስጋና
በድሉ ዋቅጅራ ሀገራችን አሉኝ ከምትላቸው ገጣሚያን እና የስነጹሁፍ ሙሁራን አንድ ነው፡፡ የወይራ ስር ጸሎትን ጨምሮ በስነጹፍ ቃንቃ ምስተምር ( የቃንቃ መቀስተማሪያ)፣ ፍካትና ናፋቂዎች ( የግጥም ስብስብ)፣እውነት ማለት የኔ ልጅ ( የግጥም ስብስብ)፣ ያልተከፈለ ስለት ( የግጥም ስብስብ )፣ የማይጻፍ ገደል ( ግለሂወታ ላይ የተመሰረቱ ታሪኮች ) የሚሉ ስምንት መጸሀፎችን ያሳተመ የስነጹፍ መምህርና ባለሙያ ነው፡፡በስራው ስራ ላይ ሂስ ለመስጠት ስንነሳ ያለውን ሙሉኡነት እና ቀርነት ማነጸሪያ የሚሆን ሳይንሳሚ ብያኔ የዘን ወደፊት ለሚጽፉ ጻሀፍት መማሪያ ይሆን ዘንድ በቅንነት ተነስተን መሆን እንዳለበት የዚህ ጹህፍ አዘጋጅ በሚገባ ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ልናሂሰው የተነሳነው ስራ ባይሰራ ኖሮ ኢሄን ጹሁፍ ማዘጋጀትም አይቻልም ነብረ ፡፡ ስለዚ ኢችን የግጥም መድብል የበረከተልንን በድሉ ዋቅጅራን በታለቅ ትህትናና አክብሮት የጹሁፉ አዘጋጅ ማመስገን ይፈልጋል ፡፡
‹‹ የርእሰ ጉዳይ አቀናቀንና የአዚያዚያም ስልት ›› በበድሉ ወቅጅራ ‹‹የወይራ ስር ጸሎት ›› የግጥም መድብል ፡፡ በሚል እርእስ በተዘጋጀው በዚ የሂስ ጹሁፍ ላይ እንደማንጸሪያ ያገቡ

12/02/2019

የሥነ-ጥበባት ኮሌጅ
የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት

"የጉለሌው ሰካራም አጭር ልቦለድ" ከስነ-ማህበረሰባዊና ከስነ-ልቦናዊ ሂስ አንጻር ሲቃኝ

ለCritics ኮርስ ማሟያነት የተሰናዳ

በ፡-
ያሬድ መኮንን

የካቲት 2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ይህ "የጉለሌው ሰካራም አጭር ልቦለድ" ከስነ-ማህበረሰባዊና ከስነ-ልቦናዊ ሂስ አንጻር ሲቃኝ "የጉለሌው ሰካራም አጭር ልቦለድ" ከስነ-ማህበረሰባዊና ከስነ-ልቦናዊ ሂስ አንጻር ሲቃኝ የተሰኘ ጽሁፍ ለስነ ሂስ ኮርስ ማሟያ ላይ የሰራሁት በማለዳ ድባብ ርዕስ ላይ የተሰራ ሲሆን አንብባችሁ ገንቢ አስተያየት እንደምትሰጡኝ በማመን ለእናንተ አጋራለሁ፡፡ መልካ ምንባብ!
ምስጋና
ይህንን ለCritics ኮርስ ማሟያነት ለመሄስ የመረጥኩትን "የጉለሌው ሰካራም" የተሰኘ አጭር ልቦለድ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጽፈውና አዘጋጅተው ለአንባብያን ያቀረቡትን ደራሲ ተመስገን ገብሬን ስለትጋታቸውና ስለፈር ቀዳጅነታቸው ምስጋናዬ ከአጸደ ነፍስ እንደሚደርሳቸው እምነቴ ነው፡፡ ደራሲ ተመስገን ገብሬ ብዙ መስራት በሚችሉበት በጎልማሳነት እድሜያቸው ከዚህች ዓለም በሞት ባይለዩ ኖሮ በርካታ መጻህፍትን ለአንባብያን ማቅረብ በቻሉ ነበር፡፡ ዳሩ ይህ የአምላክ ፈቃድ ነው፡፡ ነፍሳቸው በአጸደ ገነት ያኑር!
መቅድም

በዓለም መድረክ የአጭር ልቦለድ ጀማሪ ተደርጎ የሚወሰደው አሜሪካዊው ኤድጋር አሌንፖ መሆኑን የስነ-ጽሁፍ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ሀቅ ነው፡፡ በሀገራች የመጀመሪያው አጭር ልቦለድ ደራሲ ተመስገን ገብሬ ሲሆን፣ ድርሰቱም "የጉለሌው ሰካራም" መሆኑ ይታወቃል፡፡ ተመስገን ገብሬ የተወለደው በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በደብረ ማርቆስ ከተማ በ፲፱፻፪ዓ/ም ነው፡፡ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ የቤተ ክህነት ትምህርት ተከታትሎዋል፡፡በትምህርቱ እጅግ ጐበዝ የሚባል በመሆኑ ገና በ15 ዓመቱ የቅኔ መምህር ሆኖ ነበር፡፡ በቤተ-ክህነት ትምህርት በዚህ እድሜ የቅኔ መምህር የሆነ ሰው ከተመስገን ሌላ አልተገኘም ይባላል፡፡ ይህ ሰው በ1918 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የዘመናዊ ትምህርቱን በስዊድሽ ሚስዮን ተከታትሎ ጨርሷል፡፡ ከጎጃም ወደ አዲስ አበባም በመምጣት በስዊድን ሚሲይናዊ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ለሚሊኒየም ያሳተመው አጀንዳ እንደሚያሳየው በወቅቱ ሀገሪቱ ካፈራቻቸው ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ነበር፡፡ተመስገን በጋዜጠኝነት ሙያ ከመሥራቱም በላይ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት ቦታ ተመድቦ አገልግሏል፡፡ ተመስገን የኤርትራ ድምፅ የሚሰኝ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅም ነበር፡፡የአልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን ኃይለ ስላሴ የቤት ውስጥ መምህርም ነበር፡፡በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አጭር ልቦለድ የሚባለው የጉለሌው ሰካራም መጽሐፍም ደራሲ ነው፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ችሎታውና በአፃፃፍ ቴክኒኩ እጅግ የተዋጣለት ደራሲ መሆኑን ሃያሲያን ይናገራሉ፡፡ በ1920ዎቹ ውስጥ ጣሊያን ኢትዮጵያን ከመውረሯ በፊት ወረራው ለኢትዮጵያ እንደማይቀር በማወቅ በየደባባዩ ሕዝብን እየሰበሰበ አንድ እንዲሆንና ጠላትን እንዲመክት ያስተምር ነበር፡፡ በአንድነቷ የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመመስረት ብርቱ ትግል አድርጓል፡፡
የጉለሌው ሰካራም ከመታተሙ በፊት ስለ የካቲቱ ፋሺስታዊ ጭፍጨፋ (ግፊቱን በቀመሱት አርበኛው ደራሲ አገላለጽ፣ ‹‹ዓለም በድንገት ተለውጣ፣ አዲስ አበባም ኢጣሊያኖች ኢትዮጵያውያንንየሚያርዱበትቄራሆናነበር››) “የካቲት፲፪” በሚልርዕስእና “ሊቀ-ጠበብት እውነቱ” የተሰኙ ሁለት አጫጭር ልብ ወለዶችን በጋዜጣ ላይ አውጥተዋል፡፡[1] ከዚህም ሌላ ‹‹ሕይወቴ›› የተሰኘውን ግለ ታሪካቸውን ያዘጋጁት አርበኛው አቶ ተመስገን ገብሬ በአምስቱ ዓመት የፋሺስት ወረራ ጊዜም በደረሱት ‹‹በለው አትለውም ወይ፤የጥቁር አንበሳ አይደለህም ወይ›› በሚለው መዝሙራቸውም ይታወሳሉ፡፡
ተመስገን ኢትዮጵያ በኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት በአርበኝነት ከጠላት ጋር ተፋልሟል፡፡በኋላም ወደሱዳን ተሰዶ ገዳሪ ፍውስጥ እያለ ኢትዮጵያዊያንን በልዩልዩ መልክ አስተምሮዋል፡፡ ተመስገን ገብሬ በኢጣሊያ ወረራም በፋሽስቶች ሊገደሉ ከሚፈለጉ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒ ላይ ቦምብ ወርውረው ካቆሰሉት በኋላ ፋሽስቶች 30 ሺ ያህል የሚገመት የአዲስ አበባን ሕዝብ ጨፍጭፈዋል፡፡ ጣሊያኖች እነ አብርሀ ደቦጭ ግራዚያኒን ለመግደል ያሴሩት በተመስገን ገብሬ ግፊት ነው ብለው በማመናቸው በዋና ጠላትነት ይፈልጉ ትነበር፡፡በዚያን ወቅት ተመስገንም በአጋጣሚ በፋሽስቶች እጅ ይወድቃል፡፡ ግን ተመስገን ገብሬ መሆኑን አላወቁም፡፡ስሙን ሸሸጋቸው፡፡እሱንም ሊገድሉት እስር ቤት ባስገቡት ወቅት ጣሊያኖች ኢትዮጵያዊያኖችን ሲጨፈጭፉ በዓይኑ አይቷል፡፡ ከዚህም ጭፍጨፋ በተአምር አምልጦ ወደ ሱዳን ይሰደዳል፡፡ ተመስገን ገብሬ ይህን የየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የተደረገውን ጭፍጨፋ እና በአጠቃላይ በርሱ ሕይወት ዙሪያ ያለውን ውጣ ውረድ ሕይወቴ በሚል ርዕስ ፅፎታል፡፡ ጣሊያን ከለቀቀች በኋላ የዘመናዊ አስተሳሰብና ዕድገት ዓላማዋ ዕውን እንዲሆንም ፍፁም የለውጥ አርበኛ ሆኖ ሠርቷል። ታህሳስ 15 ቀን 1941 ዓ.ም በ40 ዓመቱ አረፈ፡፡ (ምንጭ፡የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ለሚሊኒየም ያሳተመው አጀንዳ።)
ሀተታ ዘጉለሌው ሰካራም አጭር ልቦለድ
ተመስገን ገብሬ ኅዳር ፳፪ቀን፲፱፻፵፩ዓ/ም በአዲስ አበባ ነፃነት ማተሚያ ቤት" የጉለሌው ሰካራም "በሚል ርዕስ ያሳተመው አጭር ልቦለድ ድርሰቱ የመጀመሪያው፣የታተመ የአማርኛ አጭር ልብ-ወለድ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡"የጉለሌው ሰካራም" አጭር ልቦለድ በዋናነት አንድ ታሪክን ብቻ የሚተርክ በመሆኑ በታሪኩ መጨረሻ የምናገኘው ውጤት ነጠላ ነው፡፡ ሁሉም የታሪኩ አካላት በአንድ ተሳስረው፤ ወደ አንድ ዋነኛ ትኩረት የሚፈሱበት፤ ደራሲውም በአንባብያኑ አዕምሮ ተቀርጾ እንዲቀር የፈለገው አንድ ኪነ-ጥበባዊ ግብ ነው፡፡ እርሱም ስካር የምንወደውን ነገር ሊያሳጣን ይችላል ነው፡፡ በዚህም ይህ አጭር ልቦለድ ነጠላ ውጤት እንዳለው መረዳት እንችላለን፡፡

“የጉለሌው ሰካራም” ከስነ-ምግባራዊ፣ ከስነ-ማህበረሰባዊና ከስነ-ልቦናዊ ሂስ አንጻር
ስነ-ልቦናዊ ሂስ የሰዎችን ውስጣዊ ህይወት ከሚገልጹ መርህዎች በመነሳት የደራሲውን ሆነ ገጸባሁርያቱን ውስጣዊ ህይወት መሰረቶች ፈላጎ በማግኘት ላይ ያተኩራል፡፡ አንድን ስነጽሁፍ ስራ በመመርመር የደራሲውን ማንነትና አጠቃላይ ስብዕና ለማውቅ ሚያስችሉ የስነ ልቦና መርሆችን ይመረኮዛል፡፡ ህያሲው አንድን የተወሰነ ስራ ደራሲው እንዲፈጥር አንድ ስነ ልቦናዊ ሁንታ አለ ብሎ ያምናል ስለዚህ ዋነኛው ትኩረት የህን አውጥቶ ለማሳየት ይሆናል ሲል ዘሪሁን ስፋው በየስነ-ጽሁፍ መሰረታዊ መጻፉ ገጽ 363 ላይ ያስረዳናል፡፡
የጉለሌው ሰካራም አጭር ልቦለድ በይዘቱ በዘመኑ ይኖሩ ለነበሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለይም እየሰከሩ ያስቸግሩ ለነበሩ ግለሰቦች ስነ-ልቦናዊ ጫናን በማሳደር ከስካራቸው እንዲለያዩ ታስቦ የተጻፈ ልቦለድ ይመስላል፡፡
Wilbur scott የተሰኘ የስነ-ጽሁፍ ባለሙያ በገጽ 123 ስነ-ማህበረሰባዊ የሂስ ዓይነት "ገና ከመነሻው በስነ-ጽሁፍና በማህበረሰብ መካከል ያለው ግንኙነት መሆኑንና ይህን ግንኙነት ዋና ነገር መሆኑንና ይህን ግንኙነት መመርመር ደግሞ አንድን የኪነ-ጥበብ ስራ የማጣጣምንም ሆነ የመገንዘብን ችሎታ ከፍ ያደርጋል፡፡ ብሎ ያምናል፡፡ በአዲስ አበባ ዩቢቨርሲቲ የስነ-ጽሁፍ መምህር የሆነው ዘሪሁን አስፋው በበኩል በመጸሐፉ በስነ-ጽሁፍ መሰረታውያን ገጽ 365 ላይ "አንድ የስነ-ጽሁፍ ስራ ጥንካሬውና ድክመቱ የሚለካው የማህበረሰቡን የተለያዩ መልኮች በማንጸባረቅ ደረጃው ነው…. ደራሲው የማህበረሰቡ አባል በመሆኑ በኖረበት ዘመን የታዩ የተለያዩ ማህበረሰባዊ ክንዋኔዎች እሱንም ይነኩታልና ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች ውጪ ሊሆን አይችልም ሲል ይገልጻል፡፡
የአጭር ልቦለድ ባህሪያት በ“የጉለሌው ሰካራም” አጭር ልቦለድ ውስጥ
አልበርት ኬ ሪድአመት እና ጀሴ ስቱዋርት የተባሉ የአጭር ልቦለድ ደራሲያንና መምህራን በአዘጋጁት የአጭር ልቦለድ መድብል በአብዛኛዉ ተቀባይነት የሚኖረዉ ያጭር ላቦለድ በያኔ በማለት የሚከተለዉን አስፍረዋል፡፡ በእርዉ የተጻፈ በጠበቀ አንድነት የተዋቀረ አብዛኛዉን ጊዜ ከአስር ሺ ቃአላት የማይበልጥና የፈጠራ ባህርያትን የተላበሰ ስራ ነዉ፡፡ ከአንድ ጭግር ጋር የሚጋረጥ ስለ ችግሩም ዉሳኔ መስጠት የሚገባዉ ከገባባቸዉ አጋጣሚዎች አኳያ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ድርጊቶች የሚፈጸምን አንድ ገጸባህሪ ተዉኔታዊ በሆነ አቀራረብ የሚያሳይ ነዉ፡፡
በ“የጉለሌው አጭር ልቦለድ ላይ የሚተረከው ታሪክ በርከት ያሉ የታሪክ አቀበትና ቁልቁለቶችን ሳይወጣና ሳይወዠድ ሳይጠማዘዝ ቶሎ በመተረክ፣ ትልሙና የተለያዩ ታሪኮቹ ፍሰታቸውን እንደጠበቁ የመቼት ገለጻና የገጸ-ባህሪ ዳራ ሳይሰጥ በመጓዝ መደምደሚያውን ያገኛል፡፡ ይህም "የሰው ምስጢር" የተሰኘው አጭር ልቦለድ ጥድፊያ የተሰኘውን የአጭር ልቦለድ ባህሪ እንደሚያሟላ ያሳያል፡፡
ከላይ ባጭሩ በተገለጸው በ“የጉለሌው ሰካራም" የአጭር ልቦለድ ውስጥ እንደ ምንመለከተው በታሪኩ ፍሰት ውስጥ አላባውያኑ እርስ በእርስ በሚፈጥሩት አይቀሬ ቅንጅት በቁጥብነት ተሞልቶ፤ ከሌሎች አላባውያን ጋር በመተሳሰረና እየተጣመረ ሳይንቦረቀቅ በቁጥብነት ሲጓዝ ይታያል፡፡ ይህም ከአጭር ልቦለድ ባህሪያት አንዱና ዋነኛ የሆነው ቁጥብነት በውስጥ አምቆ መያዙን ያሳያል፡፡
ከአላባዊያን አንጻር
አጭር ልቦለድ በአንድ ዋና ገጸባህሪ ህይወት ላይ በማተኮር የሱም ህይወት አንድ ዘለላ በመምረጥ ሌሎቹንም አላባውያን በዘህ ዙሪያ በማጠንጠን ወለላ ወለላዉን ያቀርባል ይህም በአንድ የትኩረት ጎዳና እንዲጓዝና በፍጥነት ወደግቡ እንዲገሰግስ ያደርገዋል፡፡ ከአጭር ልቦለድ አላባውያን መሀል "የጀርባ አጥንት" እየተባለ የሚጠራው ግጭት "በአጭር ልቦለድ መሰረታዊ ነገር ነው" ሲል ዘሪሁነ አስፋው የስነጽሁፍ መሰረታዊያን በሚል መጻፉ ከገጽ231-232 አስፍሮታል፡፡
ከመቼት አንጻር፡-
የልቦለድ ገባሃሪያት አንደ እውኑ አለም ሰዎች ታሪካቸውን የሚፈጽሙበት ታሪካዊ ጊዜ፣ ወቅት እለትና ሰአትም አላቸው፡፡ ገጸባህርያቱ በተፈጠረላቸው ሁነት ውስጥ በመንቀሳቀስ ታሪካቸውን የሚፈጽሙት በጠባብ ክልል ሲሆን ለዚህ ጠባብ ክልልም የሚሰጠው ገለጻ የተቆጠበ ነው፡፡ታሪኩ ጥቂት ሰአታት ወይም ቀናት እድሜ ያለው ሲሆን "በጣም በትንሹ ይለዋወጣል" ሲል ዘሪሁን አስፋው፤ የበአሉ ግርማ ሴቶች አምስት ይለኞች ፣ የአጭር ልቦለድ ኪነጥበብ ጥቂት ገጽታዎች እና ሌሎች 11 ስነጽሁፋዊ መጣጥፎች አ.አ.ዩ. የኢትዮያ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ ክፍል ጥር 1986 ገጽ20-21 ገልጾታል፡፡
በዚህም በጠባብ መቼት ውስጥ በሚተረከው ታሪክ ሚተላለፈው ጭብጥም እንደ ታሪክ አንድ ሊሆን እንደ ሚገባው ይናገራል የአጭር ልቦለድ መጠነርእይ ጠባብ በመሆኑ ብዙ ማህበረሰባዊ ጉዳዮችን ሊይዝ አይችልም፡፡ የተለያዩ ጉዮችን ለማሳየት የተሞከረበት ከአቅሙ በላይ ነገር ስለሚታጨቅበት ቅርጹ ይበላሻል፡፡ ጭብጡ ከነጠላ ውጥቱ ጋር በሚገባ ተቀናጅቶ የሚቀርብ በመሆኑ "ተደራቢ አብይ ጉዳይ በመልካም አጭር ላቦለድ አይኖርም" ሲል ዘሪሁን አስፋዉ በ የስነጽፈሁፍ መሰረትውያን መጻፉ በገጽ 232 አስፍሮታል፡፡
በዚህ “የጉለሌው ሰካራም"በተሰኘ አጭር ልቦለድ ውስጥ ደራሲው ውሱን መቼትን የተጠቀመ ሲሆን፤ ታሪኩ የተፈጸመው በጥቂት ቦታዎች ነው፡፡ ጊዜውም በጣም አጭር ነው፡፡ ማህበራዊ ሁኔታውም መጠነ-ርዕዪው የተገለጸበት መንገድ በጣም ውሱን ነው፡፡ ታሪኩ ነጠላ በመሆኑ፣ እንዲሁም በጥድፊያ በመጓዙ፣ ብሎም የገጸ-ባህሪያቱ ቁጥር ውስን ከመሆኑም ባሻገር እርስ በእርስ ያላቸው ግንኙነት የተመጠነ በመሆኑ ታሪኩ የፈጀው ጊዜና የተከናወነበት ቦታ ውሱን እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ከገጸ-ባህሪ አንጻር፡- በ"ጉለሌው ሰካራም" አጭር ልቦለድ ውስጥ ውሱን የሆኑ ገጸ-ባህሪያት ውስጥ የተካተቱ ሲሆን፤ በዋናነት የታሪኩ ቁልፍ የሆነው አካል ተደርገው ቀርቧል፡፡ ደራሲው ዋና ገጸ-ባህሪው ሲገልጠው "በጉለሌ የነበረው የታወቀ ዶሮ ነጋዴ ማነው ብለው ከገፈርሳ እስከ ደጃዝማች ይገዙ ሠፈር ለጠየቁ ሰዎች፤ ተበጀ፣ ሰካራሙ ተበጀ፣ ዶሮ ነጋዴው ተበጀ ነው ብለው ይነግሯቸዋል።
የሕይወቱ ታሪክ ፍጹም ገድል ነው። ጢም ያለው ሽማግሌ ሰው ነው። ራሱን ጠጉር ውሀ ወይም መቀስ ነክቶት አያውቅም። ማለዳ አይናገርም። በጠርሙስ የከመረውን ከጠጣ በኋላ ማታ ሲራገም ወይም ሲሳደብ፣ ሲፈክር ወይም ሲያቅራራ ድምጡ ከፈረንጅ ውሻ ድምጥ ይወፍራል። ቢያውቀውም ባያውቀውም ላገኘው ሁሉ ማታ ሰላምታ ይሰጣል። ቢያውቀውም ባያውቀውም ካገኘው ሁሉ ጋራ ማታ ይስቃል። ቢያውቀውም ባያውቀውም የሰላምታው አይነት እንደ ወታደር ወይም እንደ ሲቪል ቢሆን ለእርሱ እንደተመቸው ነው። ከሰላምታው ጋራ ድምጥ ትሰማለችሁ። ከአፉ ከሚወጣው ግን አንድ ቃል መለየት አትችሉም።" በማለት ይገልጠዋል፡፡ ከላይ ከቀረበው ታሪክ እንደምናየው ተበጀ የተሰኘው ገጸ ባህሪ በ3 ወይም በ4 የገጸ-ባህሪ የአሳሳል ደረጃ ያለፈ መሆኑን ነው፡፡
o ግጭት፡- በዚህ “የጉለሌው ሰካራም” በተሰኘ አጭር ልብወለድ ውስጥ የሚቀርበው የግጭት ዓይነት ስነ-ልቦናዊ የግጭት ዓይነት ነው፡፡ ከዚህም የምንረዳው ግጭት ውስጥ የገባውቡት ባለ-ወተቷና አላቢዎቹ ከግጭቱ ውስጥ ሲወጡ የወትሮዎቹ አለመሆናቸው ነው፡፡

o አጽመ-ታሪክ፡- የአጭር ልቦለድ ትልም የአጭር ልቦለድ ባህሪያትን ተላብሶ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በ"የሰው ምስጢር” አጭር ልቦለድ ውስጥ ትልሙ ሌሎቹን አላባውያን አሰናስሎ በግጭት ተገንብቶ፤ በምክንያትና ውጤት ተከታታይነት ተቀነባብሮ ታሪኩን ሲያራምድ ይስተዋላል፡፡ በባለ ወተት አጭር ልቦለድ የትልሙ ዋነኛ መሰረት በናርዶስ ውስጥ በሚፈጠረው ቅሬታ ለሚስቱ የሚኖረው ስሜትና አመለካከት
ከልቦለድ ዘዴዎች አንጻር
o አንጻር፡- የትረካውን አንጻር ስንመለከትም በዚህ አጭር ልቦለድ ደራሲው የሁሉን አወቅ/እግዜር አከል አንጻርን ተጠቅሟል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ አጭር ልቦለድ እንደ ምልልስ፣ ምልሰት፣ ልብሰቀላና ገለጻን ተጠቅሟል፡፡ እኒህን ዘዴዎች ሲጠቀም ለየ አንድ አንዳቸው እንደየ አግባባቸው የተጠቀመባቸው ሲሆን፤ ይ አጭር ልቦለድ ከሞላ ጎደል የአጭር ልቦለድ አላባውያንን ተጠቅሟል ማለት እንችላለን፡፡

ማጠቃለያ
ከላይ ከብዙ በጥቂቱ ለማንሳት እንደሞከርኩት የጉለሌው ሰካራም አጭር ልቦለድ እኔ እንደተመለከትኩትና እንደገባኝ ለማቅረብ ሞክሬአለሁ፡፡ ከኔ የተለየ ሌላ ዓይነት ምልከታ ካለ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ ባቀረብኩት ሂስ ላይ የሚነሳ ማነኛውም ሂስ ካለም በትህትና የምቀበል መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ! አመሰግናለሁ!

Address

Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ኪነ ሂስ Kine Hise posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Establishment

Send a message to ኪነ ሂስ Kine Hise:

Share