11/01/2023
አማን ሚካኤል አንዶም
°ዳኒኤል አስፋው ስለ ጀነራል አማን አንዶምን አሟሟት ለደርጉ ሪፖርት ያደረገው በዚህ መልኩ ነበር
“ ጄኔራሉ ተይዘው መጥተው እንዲታሰሩ ፤ አልያዝም ካሉ እንዲገደሉ ደርጉ አዘዘኝ፡፡ እኔም መድፈኛውን አዛዥ ሻለቃ ኃይሉ ፋንታዬን፤የወታደር ፖሊስ አዛዥ ሻምበል ስሜን እና አጅቦ የሚያመጣ ቃኝ ጦር ይዤ ወደ ጄኔራሉ ቤት ሄድኩ……. በግምት በ1950ሰዓት( ወታደራዊ አቆጣጠር) ጄኔራሉ በደርግ መፈለጋቸውን በልዩ ልዩ ምነገዶች ማስረዳት ጀመርኩ፡፡ በመጀመሪያ የቤቱን ደውል ደወልኩ እና ከቦታው ዞር አልኩ፡፡ ምንም መልስ ስለጠፋ በከፍተኛ ድምፅ ጄነራል አማን ደርጉ ዘንድ ይፈለጋሉ አልኩ፡፡ ምንም መልስ ስለሌለ ይህንኑ ሶስት ግዜ ደጋገምኩ፡፡
ሰውየው መልስ ስለከለከሉ ጄነራል አማን እጅዎን ይስጡ ባይሰጡ ይገደላሉ! ብዬ ተናገርኩ፡፡ አሁንም መልስ በመጥፋቱ ክቡር ጄነራል አምስት ደቂቃ አለዎት፤ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ባይወጡ ይተኮስብዎታል አልኩ፡፡ ከዚያም አራት ደቂቃ ብዬ ሶስት ደቂቃ ስል ወደ ሳሎን መጡና ማነው የፈለገኝ አሉ፡፡ እኔም መልሼ ደርጉ አልኳቸው ለምን አሉ፡፡ ለስራ ነው ስላቸው አንድ በግልፅ ያልሰማሁትን ነገር ተናገሩ፡፡
ከዚያም ቀጥሎ ምንም ድምፅ ስላላሰሙ እንደገና ሶስት ደቂቃ አለዎት አልኩና ወታች እቆጠርኩ 10 ሴኮንድ ከዚያም ዜሮ ሆነ ተኩስ ብዬ የፓንሀርድ ሞርታር በሩን እንዲሠበር አዘዝኩ፡፡ ሞርታሩ ተሰናከለና ለሁለት ደቂቃ ያህል ዘግይቶ መብራት ወደ በሩ እያበራ ሲተኩስ ዋናው በር ተሰብሮ ወለል ብሎ ተከፈተ፡፡ አሁንም እጅዎን ይስጡ ብል ዝም ስላሉ የፓንሀርድ መትረየስና ኮርታር ተኩስ ቀጠለና መስኮቶች ደ ምዕራብ ያሉት ሙሉ በሙሉ ተመቱ፡፡ ቀጥሎ 5ቱን የፈጥኖ ደራሽ ወታደሮች ይዤ ወደ በሩ ተጠጋሁና ጨበጣ ግቡ ስላቸው ከውጭ ብቻ እየተኮሱ ሳለ ሰውየው ከወደ መኝታ ቤት አከባቢ በኮሪደሩ ውስጥ እያሳለፉ አውቶማቲክ ተኩስ ተኮሱብን ወታደሮቹ በተኩሱ ውስጥ ለመዝለቅ ስላልሞከሩ ጄኔራሉ እየተኮሱ መሳደብና መፎከር ጀመሩ “ እኔ አማን ነኝ ፣አንበሳው አማን ነኝ አታውቀኝም” እያሉ ማስፈራራት ቀጠሉ፡፡
….. መትረየስ እንዲመጣ አዘዝኩና ከጂፕ ላይ ኤ.4 ተፈትቶ መጣ፡፡ ያመጣውን ወታደር እንዲተኩስ ባዘው መትረይስ ተኩሼ አላውቅም አለኝ፡፡ ተቀበልኩና እንዴት እንደሚተኮስ አሳይቼ ስሰጠው ተቀብሎ ምላጩን ሲጨረግድ አፈሙዙ ወደኔ ዞረ ለማምለጥ ስሞክር ከአፈሙዙ በወጣው ጥይት የቀኝ እጄን ትንሽዋ ጣት በጣም ትንሽ በሆነ ጨረፍታ ተጫረች፡፡ ወታደሩ መትሬሱንትቶ ከኪሱ ባንዴጅ አውጥቶ አሰረልኝ፡፡ እኔም መትረየሱን ተቀበልኩና በበሩና በመስኮቱ እየዞርኩ ተኩስ ብዙ ቆይቼ በመሃሉ ሻምበል ስሜ መጥቶ ወደጎፋ ሰፈር ተኩስ ይተኮሳል በጣም ከፍተኛ ተኩስ ነው አለኝ፡፡
እኔም ተኩሱን አዳምጨ ጦሩን ጎበዝ ተኩስ የሚተኮሰው ለሚገደሉት እስረኞች/ ለ59ሚኒስትሮችና ጄኔራሎች/ ስለሆነ ምንም አትደናገሩ ግዳጃችሁን ቀጥሉ አልኩና እኔም ወደ ቤቱ ተመለስኩ ከዚያም ጎበዝ ወደ ውስጥ እንግባ አልኩና መትረየሱን እየተኮስኩ ወደ ሳሎን ገባሁ፡፡ የሳሎን መብራት የሚበራ ሲሆን ሰውው ያሉበት ክፍልና ኮሪደር ጨለማ ስለሆነ የት እናዳሉ አይታወቅም መብራቱን እንዳላጠፋው የባሰ ችግር ይፈጠራል፡፡
አስር አለቃ አየለ ሃብተማሪያም የመትረየሱን ጥይት ይዞልኝ አብሮኝ ገባ፡፡ ቀጥሎም አስር አለቃ አየለ ከገበታ ቤትና ሳሎን መሃል ሆነን ስንተኩስ ተራ ወታደር በቀለ በጥይት ተመታ፡፡ ጄኔራሉ እያከታተሉ አውቶማቲክ ይተኩሱ ስለነበር ወታደር ጉዲሳ ገመዳ ወደ ቤቱ ውስጥ ገብቶ እንደገና ሊወጣ ሲሞክር በጥይት ተመታ፡፡ ሰውየው በተኩስ መልስ ወደሚሰጥበት ክፍል መትረየሱን ስተኩስ ተሰናከለ ያንን መትረየስ ትቼ ዑዚ ስተኩስ አስር አለቃ አየለ መትረየሱን አስተካክሎ መተኮስ ጀመረና ድጋሚ ተሰናከለበት፡፡ እኔም ተቀብዬ ተኩስ መተኮሱን ስላቆመ ትቼለት እሱ ሲቀበለኝ በጥይት ተመታ፡፡ በዚህ መሃል ታንክ መጥቷልና አብረህ እንዳትመታ ውጣ የሚል ጩኸት ከውጭ ስላስተጋባ በገበታ ቤቱ መስኮት ከፍቼ ዘለልኩና ወጣሁ፡፡……. ታንክ ወደቤቱ ተጠግቶ እየገፋ እንዲያፈርሰው ተደረገ……. ሰውየው በጀርባቸው ወድቀዋል። ሌሎች ገብተው ሬሳቸውን እንዲያወጡ ጠራሁ፡፡ ጄነራሉ ሞተው ሲገኙ አጠገባቸው አንድ ዑዚ ድግን መትረየስና አንድ ኮልት.38 ተገኘ…፡፡
( ህዳር 16 /1967 በኮሎኔል ዳንኤል አስፋው ከቀረበ ሪፖርት)