17/08/2025
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሱሉልታ፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች አርብ ዕለት በፈጸሙት ጥቃት፣ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ባልደረቦች የሆኑ ሶስት ሰራተኞች መገደላቸው ታወቀ።
በጥቃቱ፣ ከባንኩ ሰራተኞች በተጨማሪ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሌሎች ሰላማዊ ሰዎችም ለህልፈት መዳረጋቸውንና የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን ከስፍራው የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
በዚህ አሰቃቂ ጥቃት ህይወታቸው ያለፈው የባንኩ ሰራተኞች፦
◾ አቶ ገመቹ ጥላሁን
◾አቶ ካሳሁን እንኮሳ
◾ አቶ መሳይ አበራ መሆናቸው ታውቋል።
ሱሉልታ ከተማ፣ ለዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ባላት ቅርበት ምክንያት ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ ይደረግላታል ተብሎ ቢታሰብም፣ በተደጋጋሚ የታጣቂዎች ጥቃት ሰለባ ስትሆን ቆይታለች።
የአርብ ዕለቱ ጥቃትም፣ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ መሆኑን በድጋሚ ያሳየ ክስተት ሆኗል ሲሉ የቅርብ አስተያየት ሰጪዎች ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የሌለ ሲሆን፣ የጸጥታ ኃይሎችም በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግግለጫ አልሰጡም። ይህ ክስተት፣ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ስጋትን ፈጥሯል።