20/11/2025
ፍቅር አልባ ስኬት
ብዙዎች ብዙ ችግር እንደደረሰባቸው ይናገራሉ ነገር ግን ፍቅርን ገሸሽ አርጎ ከመኖር የበለጠ ጉዳት የለም።ፍቅር በቁስል ላይ የሚፈስ ዘይት ነው።ነገር ግን ያለ ፍቅር የአዘኑ መፅናናትን አያገኙም ልባቸው በቂም ይሻክራል ያለፍቅር የተደሰቱ እያረሩ ይስቃሉ ያለ ፍቅር የተመራመሩ የተማሩ ባለጌዎች ይሆናሉ።
ደስታም ይሸሻል፣ሀዘንም ይረሳል፣እውቀትም ይሻራል፣ሀብትም ይነጥፋል፣ጉልበትም ይከዳል፣ወዳጅም ይበተናል፣ጥረትም ከንቱ ይሆናል፣የለፉበትም የጉም ስፍር ይሆናል፣የሰሱለት ገንዘብም የሚሞት በሬ ይገዛበታል። ፍቅር ግን ፀንቶ ይኖራል።የትኛውንም ደስታ፣ የትኛውንም ሀዘን ፣የትኛውንም እውቀት፣የትኛውንም ጉልበት፣ የትኛውንም ሀብት ፣የትኛውንም ጥረት የማይሽረው መለኮታዊ አዋጅ ፍቅር ብቻ ነው።
"ትልቅ አሳ ሁንና ትንሹን አሳ ዋጠው "ይላሉ ምቾት አምላኪዎች።
"ከራስ በላይ ነፋስ" ይላሉ እራስ ወዳዶች።
"ለዚህ እሻይ ቅጠል ህዝብ አትጨነቅ" ይላሉ ስጋዊ ሙህራን።
"ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ"ይላሉ አግዚአብሔር ባለጠጋ እማይላቸው ባለጠጎች።
~''ፍቅር ግን መቀበልን ሳታስብ ቸር ሁን''ትላለች በዚህ ሰአት የአንተ እርዳታ የምታስፈልገው እርሱ ባልጀራህ ነው ትላለች።
በአደባባይ ሠውን የሚያስቁ በጓዳቸው የለቅሶ ህይወት ይገፋሉ።ሌላውን የማይረዱ አዋቂዎች በመጨረሻ ያብዳሉ።
ፍቅር ግን ሳቂታዎችን ለለቅሶ ይጋብዛል። አጉረምራሚዎችን ፍቅር ለዝማሬ ይጠራቸዋል። ከሚደረግላችሁ የተደረገላችሁ ብዙ ነው ይላቸዋል።አዋቂዎችን ሞኞች ሁኑ የሚታየዉ አለም መሠረቱ የማይታየው እግዚአብሔር ነው ይላቸዋል።
በፍቅር የሆነ ደስታ በፍቅር የሆነ ሀዘን በፍቅር የሆነ ዝማሬ በፍቅር የሆነ እውቀት በመጀመሪያ ባለቤቱን ይሠራል ከዛ ይሠራበታል።
" ስጋዌ ደስተኞች በሬሳ ላይ ማእድ የዘረጉ የመቃብር ነዋሪዎች ናቸው"።
ልታይ ልታይ ያሉ ደብቁኝ ማለታቸው አይቀርም።
ድሆችን የባረሩ ከነዚህ ድሆች ዳቦ መለመናቸው የተቀጠረ ጉዳይ ነው።
ስጋዊ ደስታ ሲበዛ መከራ በደጅ ነው።
እንግዲህ ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም እግዚአብሔር ፍቅር ነውና ።/1ኛ ዮሐ 4፣8/